ጣሳ ለመክፈት ያቃታት ልጁን ለ6 ሰዓታት ያስራበው አባት ድርጊት ቁጣ ቀሰቀሰ

በጣሳ የሚታሸግ የበሰለ ባቄላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጣሳ የሚታሸግ የበሰለ ባቄላ
ታትሟል

በልጆች አስተዳደግ አለኝ በሚለው ክህሎት የሚኩራራው አባት የተራበች የዘጠኝ ዓመት ሴት ልጁን በጣሳ የተሻገ ምግብን እራሷ ከፍታ እንድትበላ አዟት ለስድስት ሰዓታት እንድትራብ በማድረጉ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቁጣ ተቀሰቀሰ።

አባት ለልጁ ይህንን አስቸጋሪ ትዕዛዝ ከሰጠ ከስድስት ሰዓታት በኋላ ጣሳውን ለመክፈት እንደቻለችና ምግቡንም እንድትበላ እንደፈቀደላት በዊተር ላይ ካሰፈረ በኋላ ነው ተቃውሞ የገጠመው።

በድረ ገጽ ላይ የሚሰራጭ ሬዲዮ አቅራቢና ሙዚቀኛ የሆነው አባት በረሃብ የተንገላታችው ልጁ ጣሳውን መክፈት መቻሏ "ለመልካም የልጆች አስተዳደግ" ድል ነው ሲልም ገልጾ ነበር።

ነገር ግን ሌሎች ወላጆች ግለሰቡን በግዴለሽነት የወቀሱት ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ታሪኩ እውነተኛ ሳይሆን ትኩረት ለማግኘት የፈጠረው ነው ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የልጆች አስተዳደግና አያያዝን በተመለከተ የሚደረጉ ምልልሶች ከስምምነት የማይደረስባቸውና የሞቀ ክርክክር የሚደረግበት ጉዳይ ነው።

ጆን ሮዲክ የተባለው ይህ አባት ስለሴት ልጁ ይህንን ታሪክ በትዊተር ላይ ያጋራው ባለፈው ቅዳሜ ነበር። በዚህም የበሰለ ባቄላ እንዲሰራላት ስትጠይቀው ታሪኩ እንደጀመረ ገልጿል።

እሷም የጣሳ መክፈቻና የታሸገ ባቄላ ይዛ ስትመጣ የጣሳው መክፈቻ እንዴት እንደሚሰራ እንደጠየቃትና እንደማታውቅ ስትነግረው ሊያስተምራት የሚችልበት አጋጣሚ እንደተፈጠረለት ማሰቡን ተናግሯል።

በዚህ አጋጣሚ የተደሰተው አባት ልጁ "የታሸገ ጣሳ እንዴት እንደሚከፈት እንድትማር እድሉን ሰጠኋት" በማለት ጣሳውን ለመክፈት ስድስት ሰዓታት እንደወሰደባት ገልጿል።

ከብዙ ጥረትና ልፋት በኋላም በመጨረሻ ልጅቷ የታሸገውን ጠሳ ከፍታ ምግቡን ለመብላት እንደቻለች አባትየው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ገልጿል።

ይህንን የሚገልጸው የትዊተር መልዕክቶቹ ምንም እንኳን ኋላ ላይ ቢሰረዙም በፍጥነት በርካታ ሰዎች ተጋርተውት ብዙዎች "መጥፎ አስተዳደግ" በማለት አባትየውን ለድርጊቱ አውግዘውታል።

ድርጊቱ ግራ የሚያጋባ መሆኑን የገለጹ ሰዎች ሲኖሩ፤ አባት ልጁን ከማስራብ ይልቅ የጠየቀችውን እንድትመገብ ካደረገ በኋላ ጣሳን እንዴት መክፈት እንደሚቻል ማሳየት ይችል ነበር በማለት ወቅሰውታል።

ልጁ ከጣሳው ጋር ስትታገል ያሳለፈችው ስድስት ሰዓታት በሁለት የምግብ ጊዜያት መካከል ያለ ልዩነት ነው በማለት ልጅቷን እንድትራብ አድርጓታል ብለዋል።

አንዲት መምህር መሆኗል የገለጸች ሴት ደግሞ ግለሰቡ ልጁ ላይ የፈጸመው ነገር ልጆችን አንድን ነገር ለማስተማር መጥፎው መንገድ ነው ብላለች።

"ልጆች አንድን ነገር በአግባቡ መማር የሚችሉት ሳይርባቸው ነው። እንደየሁኔታው የተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎች አሉ፤ በተለይ የምናስተምረው ሰው አንድን ነገር ለማድረግ የሚቸገር ከሆነ በማሳየት መርዳት አለብን" ብላለች።

ልጆች አንድ ነገር እንዲያደርጉ ወይም እንዲማሩ ምግብን እንደ መቅጫ መጠቀም አሉታዊ ውጤት እንደሚኖረውም ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ድርጊቱን የፈጸመው አባት ጨካኝ እንደሆነ በመግለጽ ቁጣና ተቃውሞ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የገጠመው ቢሆንም ባልደረባው ግለሰቡን "አፍቃሪና ትኩረትን የሚሰጥ አባት" ሲል መስክሮለታል።

ይህንን ተከትሎ አንድ በኢንተርኔት ላይ የሚተላለፍ ሬዲዮ ድርጊቱን የፈጸመው አባትን በመቃወም የተጫወታቸውን ሙዚቃዎች እንደማያቀርብ አሳውቋል።