ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራቅ ነፍሰ ገዳይ ታጣቂዎች የሚፈልጉት አስተርጓሚዎች
"በጣም ፈርቻለሁ። ዛቻ ይደርስብኛል። በማንኛውም ሰዓት አንድ ሰው የቤቴን በር ገንጥሎ አምስት ጥይት ሊተኩስብኝ ይችላል" ይላል አሊ፟።
"አንድ ጥይት ለኔ፣ አንድ ለባለቤቴ፣ ሶስት ጥይት ደግሞ ለሶስት ሴት ልጆቼ።"
አሊ [ስሙ የተቀየረ] ለብሪታኒያ ሠራዊት አስተርጓሚ ሆኖ በመሥራቱ ምክንያት የኢራቅ ታጣቂዎች ዒላማ ሊያደርጉት ስለሚችሉ ይፈራል።
ሥራው አደገኛ እንደሆነ ቢያውቅም ለሃገሩ ካለው ፍቅር የተነሳ እንደተሳተፈ ይናገራል።
ነገር ግን ዩናይትድ ስቴትስ የኢራኑ ከፍተኛ የወታደር ሹም የሆኑት ቃሲም ሶሌማኒን እና የኢራቁን ነባር ታጣቂ አቡ ማህዲ አል-ሙሃንዲስን ስትገድል የአሊ ሥራ አደገኛነት ይበልጥ ጨመረ።
የብሪታኒያ ጦር ኢራቅን ጥሎ በመሄዱ ምክንያት ክህደት እንደተፈፀመበት ያስባል።
አሊና አሕመድ [ይሄም ስሙ የተቀየረ] አንድ ባግዳድ ውስጥ የሚገኝ ሆቴል ማንነታቸውን ደብቀው ነው ለቢቢሲ ድምፃቸውን የሰጡት።
ሁለቱም ፍራቻ ውስጥ ናቸው።
"የት ሄደን እንደምንጠለል የምናውቀው ነገር የለም። ቢቢሲን ማናገር የፈለግነው የብሪታኒያ ሕዝብና የዩኬን መንግሥት ድምፃችንን እንዲሰማን በማሰብ ነው" ይላል አሊ።
'አንድ ትልቅ ቤተሰብ'
ከሁለት ዓመት በፊት ለኢራቅ ጦር መሥራት ሲጀምሩ፤ አሁን የአንድ ትልቅ ቤተሰብ አባል ናችሁ ተብለው ነበር። ይህ ከውጭ ኃይሎች ጋር እንዲሠሩ ለእነርሱ ትልቅ ማበረታቻ ነበር።
ከእነርሱ ጋር ሌሎች ስምንት አስተርጓሚዎች ነበሩ። በአሜሪካ እየተመራ ኢስላሚክ ስቴትን [አይኤስ] ለማጥፋት ከመጣው የብሪታኒያ ልዩ ኃይል ጋር ይሠራሉ።
የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 120 ሺህ የኢራቅና ከርዲሽ ወታደሮችን አሰልጥኗል ይላል።
አስተርጓሚዎቹ የብሪታኒያ ልዑካን የኢራቅ ልዩ ኃይሎችን ሲያሰለጥኑ በማስተርጎም ይረዱ ነበር።
ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሥራቸው ከማስተርጎም የላቀ እንደነበር አሕመድ ይናገራል።
የብሪታኒያ ወታደሮች ያሉበት አካባቢ ደህንነት ካሰጋቸው ወጣ ብለው አካባቢውን በመቃኘት ይረዷቸው እንደነበርና በዚህም ኩራት እንደሚሰማው አሕመድ ይናገራል።
"እነሱ 'ተዉ ራሳችሁን አደጋ ላይ አትጣሉ' ሲሉን እኛ ደግሞ 'ወንድሞቻችን ናችሁ፤ ደህንነታችን መጠበቅ እንፈልጋለን' እንላቸው ነበር።"
"እኛ ሃገራችንን እንወዳለን። እነሱ ደግሞ ሃገራችንን ለማገዝ ነው የመጡት። ለእኛ ከእነርሱ ጋር መሥራት ክብር ነበር።"
ዒላማዎች'
ነገር ግን ባለፈው ጥር ሁሉም ነገር ተቀየረ።
በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ መሠረት ኃያሉ የኢራን ሠራዊት አዛዥ ቃሲም ሶሌማኒ ተገደሉ። እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የኢራቅ አጋራቸው አቡ ማህዲ አል-ሙሃንዲስም እንዲሁ በአሜሪካ ተገደሉ።
ይህ ጉዳይ በኢራን የሚደገፉትን የኢራቅ ታጣቂዎችን አስቆጣ።
ይሄኔ ኢራቅ ውስጥ በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይል ወታደራዊ ካምፖችና ከእነርሱ ጋር የሚሠሩ ሰዎች ዒላማዎች ሆኑ።
"ሁኔታው በጣም አስጨናቂ መሆን ጀመረ። ሌላው ቀርቶ ከጥምር ኃይሉ ጋር የሚሠሩ የኢራቅ ወታደሮች እንደ ጠላት ያዩን ጀመር" ይላል አሊ።
'መንፈሳዊ ታጣቂዎች'
ማንነታቸው የማይታወቅ ታጣቂዎች ከጥምር ኃይሉ ጋር የሚሠሩ ኢራቃዊያን በፍጥነት ሥራቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቅ ጀመሩ።
ከእነዚህ ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንደኛው አሻብ አል ካህፍ የተሰኘው ነው። ይህ ቡድን የጥምር ኃይሉ ካምፖች ላይ ለተሰነዘሩ በርካታ የሚሳዔል ጥቃቶች ኃላፊነት ወስዷል።
በባግዳድ የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ለደረሰው ጥቃትም ኃላፊነት የወሰደ ቡድን ነው።
ቡድኑ በቴሌግራም በአሜሪካ ከሚመራው ጥምር ኃይል ጋር ለሚሠሩ አስተርጓሚዎች የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገባ።
"ዛሬ ከአሜሪካ፣ ብሪታኒያና ሌሎች የኢራቅ ጠላቶች ጋር በመሥራት ራሳቸውንና ሃገራቸውን ለከዱ ሰዎች ይቅርታ አድርገናል። መጥታችሁ እኛን የምታገኙን ከሆነ ወርሃዊ ደመወዝ እንሰጣችኋለን" ይላል መልዕክቱ።
ታጣቂዎች 'ደመወዝ' ያሉት የገንዘብ መጠን ለአስተርጓሚዎች 3 ሺህ ዶላር ሲሆን የአሜሪካና ብሪታኒያ ወታደሮችን በደህንነት ጉዳይ ለሚያግዙ ደግሞ 5 ሺህ ዶላር ነው።
አሕመድ ግን የመልዕክቱ ቅኔ 'ከኛ ጋር የማትሠሩ ከሆነ ጠላቶቻችን ናችሁ' ነው ይላል።
ጥቃቶች
ከሶሌማኒ ግድያ በኋላ የጥምር ኃይሉን ዕቃዎች ጭነው በኢራቅ ጎዳናዎች የሚሽከረከሩ መኪናዎች የጥቃት ሰለባ መሆን ጀመሩ።
ማንነታቸው የማይታወቀው ታጣቂዎች ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ በማሕበራዊ ድር አምባዎቻቸው የጥቃቱን ቪድዮ ይለጥፋሉ።
ነገር ግን ብዙ ጊዜ የጥምር ኃይሉን ዕቃዎች ጭነው የሚመላለሱ መኪናዎች ውስጥ ኢራቃዊያን እንጂ የአሜሪካም ሆነ የብሪታኒያ ወታደሮች አይገኙም።
"ይሄኔ ነው ዛቻዎቻቸውን ወደ ተግባር መቀየር መጀመራቸውን የተረዳነው" ይላል አሕመድ።
ነገር ግን አስተርጓሚዎቹ ሥራቸውን አላቋረጡም። ሥራው አደገኛ ቢሆንም ከሌላው የተሻለ ከለላ እንዳላቸው ይሰማቸው ነበር።
"ከሚስቴ ውጭ ማንም ሰው የት እንደምሰራ አያውቅም። ልጆቼም ምንም አያውቁም። ሚስቴም ብትሆን የት እንደምሰራ ታውቃለች እንጂ ምን እንደምሠራ አታውቅም" ይላል አሊ።
"በእንቅርት ላይ. . . "
ኮሮናቫይረስ ወደ ኢራቅ ሲገባ ሃገሪቱ ሙሉ በሙሉ ተዘጋች። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ መጓዝ የፈለገ ከኢራቅ መንግሥት ፈቃድ መያዝ ይኖርበታል።
አስተርጓሚዎቹ መረጃዎቻቸው በኢራቅ ታጣቂዎች እጅ እንደወደቀ ያምናሉ።
ቢቢሲ ያየው የስም ዝርዝር እንደሚያሳየው የስምንቱም አስተርጓሚዎች ሙሉ ስም፣ የሥራ ድርሻ፣ የመታወቂያ ቁጥር እና የመኪና ታርጋ ቁጥር ወረቀቱ ላይ ተካትቷል።
ስምንቱ አስተርጓሚዎች ሙሉ መረጃዎቻቸው በኮሮናቫይረስ ወቅት ለመዘዋወር እንዲያመቻቸው ለኢራቅ መንግሥት ወታደሮች እንደተላኩ ሲሰሙ ሁሉም ነገር ተዘበራረቀባቸው።
"ይህ ማለት ታጣቂዎቹ ስለ እኛ አወቁ ማለት ነው" ይላል አሕመድ።
በኮቪድ እና በታጣቂዎች ጥቃት መካከል ያለው ጥምር ኃይል ካምፖቹን ለኢራቅ ወታደሮች ማስከረብ ጀመረ። ኃይሉ ከመጋቢት ጀምሮ ስምንት ካምፖችን ለኢራቅ ሰጥቷል፤ የወታደሮቹን ቁጥርም በብዙ ቀንሷል።
ከእነዚህ የወታደር ካምፖች መካከል አንደኛው እነ አሊ የሚሠሩበት ነው። አብረዋቸው የሚሠሩ የብሪታኒያ ወታደሮችም ካሰቡት ጊዜ ቀድመው ጓዛቸውን ሸክፈው ኢራቅን ጥለው ወጡ።
አሁን አሊና አሕመድ፤ እንዲሁም ሌሎች ስድስት ጓደኞቻቸው ሥራ አጥ ሆኑ። አልፎም ደህንነታቸው አደጋ ላይ ነው።
ይህ ሁኔታ ቤተሰቦቻቸውን ወደ ሌላ አድራሻ ወስደው እንዲደብቁ አስገደዳቸው።
አሊ ይሄ ጊዜያዊ መፍትሄ ነው፤ በሂደት ታጣቂዎቹ ሊደርሱብን ይችላሉ የሚል ስጋት አለው።
"ልቤን በአንድ እንሥራ ታቅፌ እንደምዞር ነው የሚሰማኝ። ድንገት አደናቅፎኝ ብወድቅ ሞትኩኝ ማለት ነው" ይላል አሊ።
ግላዊ መረጃ
ቢቢሲ የጥምር ኃይሉን ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ኬቭ ኮፕሲን የአስተርጓሚዎቹ ግላዊ መረጃ ተላልፎ ተሰጥቷል ወይ ብሎ ጠይቋል።
ምክትል አዛዡ የአስተርጓሚዎቹ ግላዊ መረጃ ተላልፎ አልተሰጠም ይላሉ።
ነገር ግን ቢቢሲ የስም ዝርዝር ያለበትን መረጃ እንደተለመከተ የተነገራቸው ጄኔራሉ 'ጉዳዩን እናጣራለን' ብለዋል።
የብሪታኒያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ለቢቢሲ አሳውቋል።
ወረቀቱ በባግዳድ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ማሕተም አለበት።
ቢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ መልስ እንዲሰጥ የአሜሪካ ኤምባሲን ጠይቋል።
ኤምባሲው ከኢራቅ መንግሥት ጋር ባሉ ውስጣዊ ግንኙነቶች ዙሪያ አስተያየት እንደማይሰጥ አስታውቋል። ነገር ግን ኢራቅ ውስጥ ያለ ልዑካን ደህንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ነው ይላል የኤምባሲው ቃል አቀባይ ምላሽ።
ኢራቅ ውስጥ በአስተርጓሚነት መሥራት ከፈንጂ አምካኝነት በላይ አደጋ አለው።
ከሳዳም ሁሴን ውድቀት በኋላ ባለው ጊዜ ኢራቅ ውስጥ ላሉ የብሪታኒያ ወታደሮች የሰሩ 40 አስተርጓሚዎች ተገድለዋል።
ነገር ግን ዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን ድረስ ለእነዚህ አስተርጓሚዎች ቪዛ መስጠት አልቻለችም።
አሊና ሞሐመድም ስማቸው ከተገደሉ አስተርጓሚዎች ተርታ እንዳይሰለፍ ስጋት አላቸው።