ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አውስራሊያ ነባር ሕዝቦቿን ለማካተት ብሔራዊ መዝሙሯ ላይ ለውጥ አደረገች
አውስትራሊያ ከዛሬ [ከአዲሱ የፈረንጆች ዓመት] ጀምሮ ብሔራዊ መዝሙሯ ላይ ለውጥ ማድረጓን ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አስታወቁ።
ለዚህም የቀድሞው ብሔራዊ መዝሙር የተወሰኑ ቃላቶች ላይ ለውጥ መደረጉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
አዲሱ ብሔራዊ መዝሙር ከአሁን በኋላ በአውስትራሊያ ብሔራዊ መዝሙር ውስጥ "አዲሲቷ ነጻ አገር" የሚል አገላለጽ አይኖርም ተብሏል።
ይህ የሆነውም የአውስትራሊያን ቀደምት ሕዝቦች እና ታሪካቸውን ለማካታተት በሚል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ውሳኔ በርካቶችን ቢያስደንቅም ነገር ግን በበጎ መቀበላቸውን እና ለውጡም "የአንድነት መንፈሱን" ያጠናክራል ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
አውስትራሊያ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ ነጭ ሰፋሪዎች በቅኝ ግዛት ከመያዟ በፊት ቀደምት ሕዝቦች ይኖሩባት ነበር።
በአውስትራሊያ ሕዝብ መዝሙር ውስጥ የነበረው "አዲሲቷ ነጻ አገር" በሚለው ስንኝ ምትክም "አንድና ነጻ ሕዝቦች ነን" በሚል ተተክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የስንኝ ለውጥ የሚቀንሰው ነገር የለም ካሉ በኋላ፣ ነገር ግን "ብዙ ነገር ይጨምራል" ብለዋል።
"እንደ አገር ብዙ ርቀት ተጉዘናል። የአገራችን ታሪክ ከ300 የተለያየ ቀደምት ብሔሮች እና ቋንቋዎች የተዋጀ መሆኑንና በምድር ላይ ውጤታማ ኅብረ ብሔራዊ አገር መሆናችንን ይናገራል።"
አክለውም ለውጡ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የታየውን አንድነት እንደሚያከብር ገልፀዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው አንቶኒ አልባኔዝ፣ በለውጡ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ "በምድር ላይ ጥንታዊ እና ቀጣይነት ያለው ሥልጣኔ ባለቤቶች በመሆናችን ልንኮራ ይገባል" ብለዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አውስትራሊያ የነባር ሕዝቦችን ታሪክ፣ ባህል እና የፖለቲካ ተሳትፎ እውቅና እንድትሰጥ የተለያየ ግፊቶች ሲደረጉ ነበር።
በታኅሣስ ወር የራግቢ ተጫዋቾች ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ መዝሙሩን በእንግሊዝኛ ከመዘመራቸው በፊት፣ በኤኦራ ብሔር ቋንቋ መዘመራቸው ተነግሯል።
እነዚህ ብሔሮች ሲድኒ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው ተብሏል።