የሴቶች ጥቃት፡ ሩስያዊው ታሪክ አጥኚ ተማሪው የነበረች ፍቅረኛውን በመግደሉ ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩስያዊው ታሪክ አጥኚ ተማሪው እንዲሁም የፍቅር አጋሩን ተኩሶ ከገደለ በኋላ ሰውነቷን በመቆራረጡ የ12 ዓመት ተኩል እስራት ተፈረደበት።
የ63 ዓመቱ ኦሌግ ሶኮሎቭ የናፖሊዮን ጦርነቶች ምሁር ሲሆን፤ ግድያውን መፈጸሙን አምኗል።
ግለሰቡ እአአ 2019 ጥቅምት ላይ ሰክሮ ወንዝ ውስጥ ወድቆ ነበር የተገኘው። በቦርሳው የ24 ዓመቷ የፍቅር አጋሩ አንስቴዥያ የሾቼንኮን ክንድ ቆርጦ ይዞ ነበር።
የሴቶች መብት ተሟጋቾች የታሪክ አጥኚው ጉዳይ የተያዘበት መንገድ ሩስያ ውስጥ የቤት ውስጥ ጥቃትና ወሲባዊ ጥቃት እምብዛም ትኩረት እንዳልተሰጠው ማሳያ ነው ብለዋል።
በድረ ገጽ 7,500 ሰዎች ፊርማ አሰባስበው ሴንት ፒተርስበርግ ስቴት ዩኒቨርስቲ በታሪክ ምሁሩ ላይ በተደጋጋሚ የቀረበውን ቅሬታ ችላ ብሏል ሲሉ ወቅሰዋል።
ኦሌግ ሶኮሎቭ ከዩኒቨርስቲው እንዲሁም ፈረንሳይ ከነበረ ኃላፊነቱም ተነስቷል።
ፍርድ ቤት ሲቀርብ አንስቴዥያን አራት ጊዜ ተኩሶ መግደሉን፣ ከዚያም ሰውነቷን በስለት መቆራረጡን አምኗል።
ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሲያውለው በቦርሳው ከተገኘው የአንስቴዥያ የሰውነት ክፍል በተጨማሪ ሌላም አካሏ በግለሰቡ ቤት ውስጥ ተገኝቷል።
የአንስቴዥያን ሰውነት ሰውሮ ሲያበቃ፣ እንደ ናፖሊዮን ለብሶ ራሱን ሊያጠፋ እየተዘጋጀ እንደነበር ተነግሯል።
አንስቴዥያ ከደቡብ ሩስያ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ነበር የሄደችው።
አንድ ጓደኛው ለሩስያው አርኤንኤ እንደተናገረችው አንስቴዥያ "ጎበዝ ተማሪና ተወዳጅ ሰው" ነበረች።
እናቷ ፖሊስ፣ አባቷ ደግሞ መምህር ናቸው።
የቤተሰቡ ጠበቃ አሌክሳንድራ ባክሼቫ "ምንም ያህል እስር ቢፈረድ እሷን አይመልሳትም" ብለዋል።
የታሪክ ምሁሩ እና አንስቴዥያ ላለፉት ሦስት ዓመታት አብረው ኖረዋል።
የናፖሊዮንን ታሪክ የሚቃኝ ተውኔት አዘጋጅቶ እሱ ናፖሊዮንን ሆኖ ሲተውን እሷም ተሳትፋ ነበር።
ከጥናቶቹ መካከል ከሷ ጋር በጋራ የጻፈውም ይገኝበታል።
ከአንስቴዥያ ጋር ጸብ ውስጥ ገብተው ሳለ በስለት ልትወጋው ስትል እንደተኮሰባት ለፍርድ ቤት ተናግሯል።












