ጋዜጠኛውን ቀልቷል የተባለው ግለሰብ ከወራት በኋላ ከእሥር ተለቀቀ

ታትሟል

የፓኪስታ ፍርድ ቤት አሜሪካዊውን ጋዜጠኛ ገድሏል ተብሎ የተከሰሰው ግለሰብ ከእሥር እንዲለቀቀ አዟል።

ብሪታኒያ የተወለደው ታጣቂ ኦማር ሸይኽ በፈረንጆቹ 2002 የዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጠኛ የሆነውን ዳንኤል ፐርልን ገድሏል ተብሎ እሥር ላይ ነበር።

ነገር ግን ከወራት በፊት ነፃ ነህ ተብሎ እንዲለቀቅ ቢወሰንለትም ሳይፈታ ቆይቷል።

ካራቺ የሚገኝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰውዬው እሥር ላይ መቆየት ሕጋዊ አይደለም ሲል እንዲለቀቅ ወስኗል።

የኦማር ጠበቃ ደንበኛው በሚቀጥሉት ሰዓታት ሊለቀቅ እንደሚችል አስታውቋል።

ዳንኤል ፐርል ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በደቡባዊ ካራቺ በአሰቃቂ ሁኔታ አንገቱ ተቀልቶ ነበር የተገደለው።

ኦማር ከጋዜጠኛው መገደል ቀናት በኋላ ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው።

አንድ የፀረ ሽብር ፍርድ ቤት ኦማር ጋዜጠኛውን ገድሏል ሲል በሞት እንዲቀጣ ወስኖበታል። ኦማር የሞት ፍርዱን እየተጠባበቀ ቆይቷል።

ነገር ግን ባለፈው ጥቅምት የሲንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኦማርን ክስ ወደ አፈና በማውረድ እሱና ሌሎች ሶስት ሰዎች በነፃ እንዲሰናበቱ በየነ።

የዳንኤል ቤተሰቦችና የፓሊስታን መንግሥት ይህን በመቃወም ይግባኝ ጠይቀዋል።

ይግባኙ ምላሽ ሳያገኝ ኦማር እንዴት ሊለበቅ ይችላል የሚለው ጥያቄ እስካሁን ድረስ መልስ አላገኘም።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቃውሟል።

ለዳንዔል ቤተሰቦች እርዳታ ማድረግ እንቀጥላለን ያለው ሚኒስቴሩ "ዳንዔል እጅግ ደፋር የሆነ ጋዜጠኛ ነው። ይህን ተግባሩን ሁሌም እናከብርለታን" ብሏል።

ዳንዔል ምን አጋጠመው?

የዎል ስትሪት ጆርናል የደቡብ እስያ ቢሮ ኃላፊ የነበረው ዳንዔል ፐርል ጥር 2002 [በፈንጆቹ] አድራሻው ጠፋ።

ጋዜጠኛው በወቅቱ አንድ ዘገባ ለመሥራት ወዲያ ወዲህ እያለ ነበር።

ሪቻርድ ሪድ የተባለው ግለሰብ በጫማው ደብቆ ቦምብ ወደ አውሮፕላን በማስገባት ለማፈንዳት ሞክሮ ነበር። በዚህ ግለሰብና በፓኪስታን በሚንቀሳቀሱ እስላማዊ ታጣቂዎች መካከል ግንኙነት ይኖር ይሆን የሚለውን ለማጣራት እየጣረ ነበር።

አቃቤ ሕግ ኦማር ጋዜጠኛውን ከአንድ የእስልምና አባት ጋር ላገናኝህ ብሎ አታሎታል ሲል ይከሳል።

ኦማርና ዳንዔል በወቅቱ ሁለቱም ነፍሰ ጡር ስለነበሩ ሚስቶቻቸው እያወሩ ተቀራርበው ነበር ይላል አቃቤ ሕግ።

ዳንዔል እንደጠፋ የፓኪስታንና የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ከአንድ የፓኪስታን ቡድን ኢሜይል ደርሷቸው ነበር። ቡድኑ ቅደመ ሁኔታዎች በዝርዝር የተቀመጡበት ደብዳቤ ነበር የላከው።

ከቅደመ ሁኔታዎቹ መካከል አንደኛው አሜሪካ ውስጥ ያሉ ፓኪስታናዊ እሥረኞች እንክብካቤ እንዲደርግላቸው የሚጠይቅ ነው።

ከአንድ ወር በኋላ የ38 ዓመቱ ጋዜጠኛ አንገቱ ሲቀላ የሚያሳይ የቪድዮ መልዕክት በካራቺ ለአሜሪካ ቆንስላ ፅ/ቤት ተላከ።

ኦማር ሸይኽ ማነው?

በፈረንጆቹ 1973 ለንደን ውስጥ የተወለደው ኦማር ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኒሚክስ ተምሯል። ነገር ግን ትምህርቱን ጨርሶ አልተመረቀም።

ከመጀመሪያ ዓመት ትምህርት በኋላ ወደ ቦስኒያ አቅንቶ በዚያው ቀረ።

በ1994 አራት ጎብኝዎችን በማፈን ወንጀል እጁ አለበት ተብሎ ሕንድ ውስጥ ታሠረ። ጎብኝዎቹ ሶስቱ ብሪታኒያዊያንን ሲሆኑ አንዱ አሜሪካዊ ነበር።

በ1999 አንድ ታጣቂ ቡድን አውሮፕላን ከጠለፈ በኋላ እሥረኞች ይለቀቁ ብሎ ሲጠይቅ ከተለቀቁት መካከል አንዱ ኦማር ነበር።

አሜሪካ፤ ኦማር ከመስከረም አስራአንዱ [9/11] ጥቃት ለአንድ ታጣቂ ገንዘብ አስተላልፏል ስትል ትከሳለች።