ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶናልድ ትራምፕ፡ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ለ15 ፍርደኞች ምህረት አደረጉ
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ለአሜሪካ የምርመራ ቢሮ የሀሰት ቃል በመስጠታቸው ጥፋተኛ የተባሉ ሁለት ግለሰቦችን ጨምሮ ለ15 ሰዎች ምህረት ማድረጋቸው ተገለፀ።
የቀድሞ የምርጫ ዘመቻው ረዳት ጆርጅ ፓፓዶፑሎስ እና ጠበቃ አሌክስ ቫን ደር ዝዋን የፕሬዚደንቱን ምህረት ካገኙ ግለሰቦች መካከል ይገኙበታል።
ትራምፕ በ2007 በኢራቅ በተፈፀመው ጭፍጨፋ በመሳተፋቸው ጥፋተኛ ለተባሉ አራት የደህንነት ጠባቂዎች እና ልሁለት የቀድሞ የኮንግረስ አባልም ምህረት አድርገዋል።
ፕሬዚደንቱ በሚቀጥለው ወር ዋይት ሃውስን ለቅቀው ከመውጣታቸው በፊትም ተጨማሪ ምህረቶችን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ተሰናባች ፕሬዚደንቶች ያላቸውን መብት በመጠቀም በተለያየ ምክንያት ለተፈረደባቸው ግለሰቦች ምህረት ማድረግ የተለመደ ነው።
ጆርጅ ፓፓዶፖሎስ እና አሌክስ ቫን ደር ዝዋን አጭር ጊዜ በእስር አሳልፈዋል።
ፓፓዶፖሎስ ከአራት ዓመታት በፊት በተካሄደው ምርጫ ወቅት የሩሲያ ምርመራ አካል ናቸው ተብለው ከሚጠረጠሩ ግለሰቦች ጋር የተገናኙበትን ጊዜ ለአሜሪካ የምርመራ ቢሮ በሀሰት በመናገሩ ጥፋተኛ የተባለው ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር።
ግለሰቡ በልዩ ካውንስል ሮበርት ሙለር በተመራውና ከሩሲያ ምርመራ ጋር ተያይዞ ለእስር የተዳረገ የመጀመሪያው የቀድሞ የትራምፕ ረዳት ነው።
ሮበርት ሙለር ሩስያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች ወይስ አልገባችም የሚለውን አጀንዳ የሚያጣሩ ግለሰብ ነበሩ። ታዲያ በአውሮፓውያኑ 2016 መባቻ ላይ ነበር የሙለር ቢሮ ሩስያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ሳትገባ አትቀርም የሚለውን ጉዳይ ለማጣራት ሥራውን የጀመረው።
ይህ ልዩ አጣሪ ኃይል ሩስያ በይነ-መረብን ተጠቅማ ምርጫው ላይ ጫና አሳድራ እንደሆነ የሚያጣራ ክንፍ የነበረው ነው።
ፓፓዶፖሎስም ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁለት ግለሰቦች ጋር የተገናኘው ለዶናልድ ትራምፕ ዘመቻ ከመስራቱ በፊት እንደሆነ ተናግሮ ነበር።
በኋላ ላይ ግን ያገኛቸው ከትራምፕ ጋር መስራት ከጀመረ በኋላ እንደነበር ተደርሶበታል። ጥፋተኛ የተባለውም በዚህ የሀሰት ንግግሩ ነበር ።
ምህረቱን አስመልክቶም በትዊተር ገጹ ላይ "ምህረቱ ለእኔም ሆነ ለቤተሰቦቼ ዓለም ነው" ሲል ለፕሬዚደንቱ ምስጋናውን ገልጿል።
ቫን ዴር ዝዋን በበኩሉ በሙለር በሚመራው የሩሲያ ምርመራ ወቅት ሐሰተኛ መረጃ መስጠቱን አምኗል። ትራምፕ በተደጋጋሚ የሙለርን ምርመራ 'ሆነ ተብሎ የተፈበረከ ውሸት' ሲሉ አጣጥለውት ነበር።
ምህረቱን አስመልክቶ ዋይት ሃውስ ባወጣው መግለጫም " የዛሬው ምህረት የሙለር ቡድን በበርካታ ሰዎች ላይ የፈጠረውን ችግር ለማስተካከል ይረዳል" ብሏል።
ፕሬዚደንት ትራምፕ ለቀድሞ የሪፐብሊካን ሕግ አውጭ ክሪስ ኮሊን እና ዱንካን ሃንተርም ምህረት አድርገውላቸዋል።
የቀድሞው የኒውዮርክ የኮንግረስ አባልና የትራምፕ ታማኝ ደጋፊ ኮሊን፤ ከሕገ ወጥ ንግድ ጋር ተያይዞ ጥፋተኛ የተባሉት ባለፈው ዓመት ነበር። 26 ወራትንም በእስር አሳልፈዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የቀድሞ የካሊፎርኒያ የኮንግረስ አባል ሀንተርም የዘመቻ ገንዘብን ያለ አግባብ በመጠቀም 11 ወር በእስር እንዲያሳልፉ ተፈርዶባቸው ነበር።
አራት የቀድሞ የአሜሪካ የግል የጦር ማሰልጠኛ 'ብላክዋተር' ጸጥታ አስከባሪ የሆኑት ኒኮላስ ስላተን፣ ፖል ስላፍ፣ ኢቫን ሊበርቲይ እና ደስቲን ኸርድም በፕሬዚደንቱ ምህረት ከተደረገላቸው መካከል ይገኙበታል።
ግለሰቦቹ በአሜሪካ የፌደራል ዳኛ ጥፋተኛ የተባሉት በኢራቅ ዋና መዲና ባግዳድ፣ 14 ኢራቃዊያን ሰለማዊ ሰዎችን ተኩሰው በመግደል ሲሆን፤ ይህ የሆነውም ከ13 ዓመታት በፊት ነበር።
ፕሬዚደንት ትራምፕ ለ15 ሰዎች ሙሉ ምህረት ከማድረግ በተጨማሪ የሌሎች 5 ሰዎችን ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል ቀይረዋል።
ባለፈው ወር ፕሬዚደንት ትራምፕ ለአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ በመዋሸት ጥፋተኛ ለተባሉት የቀድሞ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክል ፍልይን ይቅርታ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ እንደ ፒው የምርምር ማዕከል፤ ፕሬዚደንት ትራምፕ ያላቸውን መብት በመጠቀም ምህረት ለማድረግ ከዚህ ቀደም ከነበሩ መንግሥታት አንፃር ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ነበር።
ከሦስት ዓመታት በፊት በትራምፕ የተተኩት የቀድሞው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ለ212 ሰዎች ምህረት እና ለ1 ሺህ 715 ሰዎች የቅጣት ማሻሻያ አድርገዋል።
ይህም በአውሮፓዊያኑ 1940ዎቹና 1950 ዎቹ በፕሬዚደንት ሃሪ ትሩማን ከተደረገው ምህረት ከፍተኛ ነው። በአንፃሩ ፕሬዚደንት ዶናልድ እስካሁን ያደረጓቸው ምህረቶች ከ40 በላይ ናቸው።