የፓሪስ ከተማ ባለስልጣናት በርካታ ሴቶችን በመቅጠራቸው ተቀጡ

የፓሪስ ከተማ ከንቲባ አኔ ሂዳልጎ በመቀጣቴ "ደስተኛ" ነኝ ብለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፓሪስ ከተማ ከንቲባ አኔ ሂዳልጎ በመቀጣቴ "ደስተኛ" ነኝ ብለዋል
ታትሟል

የፓሪስ ከተማ ከንቲባ አኔ ሂዳልጎ ለከፍተኛ ኃላፊነት በርካታ ሴቶችን በመቅጠራቸው ሕግ ጥሰዋል በመባላቸው ተሳለቁ።

እኤአ በ2018 አስራ አንድ ሴትና አምስት ወንድ በመቅጠራቸው በ2013 የወጣውን የጾታ እኩልነት ለማምጣት የተደነገገውን መመሪያ ጥሰዋል ተብሏል።

የፓሪስ ባለስልጣናት ይህንን ሕግ በመጣሳቸው ብቻ 109 ሺህ የአሜሪካ ዶላር አልያም 90 ሺህ ዮሮ በሕዝብ አገልግሎት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በኩል ተቀጥተዋል።

በ2013 የወጣው መመሪያ ለአንድ የሕዝብ አገልግሎት አስተዳደራዊ መደብ በተመሳሳይ ጾታ የሚያዘው ከ60 በመቶ መብለጥ የለበትም ሲል ይደነግጋል። የፓሪስ ከተማ ከንቲባዋ አኔ ሂዳልጎ ለሴቶች የሰጡት ሹመት ግን በመቶኛ ሲሰላ 69 በመቶ ሆኗል።

ሶሻሊስት የሆኑት ከንቲባዋ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ " የከተማዋ ምክር ቤት በድንገት በጣም ፌሚኒስት ሆነ" ሲሉ ተሳልቀዋል።

ነገር ግን በዚሁ ንግግራቸው በፈረንሳይ ወደ ከፍተኛ የኃላፊነት ስፍራ ሴቶችን ማምጣት አሁንም ቀርፋፋ መሆኑን አንስተዋል። ለዚህም መፍትሄ ብለው ያቀረቡት ከወንዶች ይልቅ በርካታ ሴቶችን መሾም ነው።

"ይህ ቅጣት፣ ገራሚ ነው፣ ፍትሃዊ አይደለም፣ ኃላፊነት የጎደለውና አደገኛም ነው" ብለዋል።

የፈረንሳይ የሕዝብ አገልግሎት ሚኒስትር አሜሊ ዲ ሞንቻሊን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ከ2018 ጀምሮ ሕጉ መሻሻሉን በማንሳት ምላሽ ሰጥተዋል።

በ2019 አጠቃላይ ያለው የጾታ ስብጥር እስካልተጎዳ ድረስ በርካታ ሴቶችን ወይንም ወንዶችን በመሾም የሚጣለው ቅጣት ተቀንሷል።

ሚኒስትሯ አክለውም ከንቲባዋን በሕዝብ አገልግሎት ስፍራዎች ሴቶችን እንዴት ማሳደግ እንደሚገባ ተገናኝተው እንዲነጋገሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ቅጣቱም "ወደ ተጨባጭ ተግባር" የሚሄድ ነው ብለዋል።