የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች እንዲጨምር አደረገ

የምትሮጥ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በከሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስሪያ መተግበሪያዎች ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመሩ ተገለፀ።

አሁን 73 ሚሊየን ተጠቃሚ ያለው ስትራቫ፣ እንዳለው ከሆነ በዚህ ዓመት በየወሩ በአማካኝ ሁለት ሚሊዮን የመጀመሪያ ጊዜ ተጠቃሚዎች መመዝገባቸው ተገልጿል።

መተግበሪያው ልምምድን ለመቅረጽ እና ያሉበትን አቋም ከሌሎች ለማነጻጸር እንዲቻል የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ይጠቀማል።

ይህ በእንዲህ እያለ በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ 90 ሺህ ተጠቃሚዎች ያሉት ፍሪሌቲክስ፣ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በመጋቢትና በሰኔ ወር በ50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የብሪቲሽ የስነልቦና ማሕበር ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቻርሎቴ ሒልተን "ኮቪድ-19 በርካታ ሰዎችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እድል ፈጥሯል። ምክንያቱም በተግባር ሰዎች እንቅስቃሴ ላለማድረግ ያላቸው ምክንያት እጅግኑ ያነሰ ነው" ብለዋል።

ከቤት ውጪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በርካታ ጊዜ በቤት ውስጥ ተዘግቶ ከመቀመጥ "እፎይታ" የሚሰጥ ነው ሲሉ ያክላሉ።

"ይሁን እንጂ በኮቪድ-19 ምክንያት በማሕበራዊ ግንኙነት ላይ በተጣለው ገደብ የተነሳ፣ ፍላጎት ያላቸው ወደ ኦንላየን ማህበረሰብ ጎራ ይላሉ። እንዲሁም መተግበሪያው ተመሳሳይ አመለካከት ካላቸው ጋር ግንኙነት በመፍጠር አካል ብቃት እንቅስቃሴውን እንዲወዱት ያደርጋል።"

ስትራቫ በመተግበሪያው የተሰሩ እንደ ብስክሌትና ሩጫ ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች መጨመራቸውን አስተውሏል።

ከዚህ ቀደም መተግበሪያውን ይጠቀሙ የነበሩ ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን በ13 በመቶ ጨምረው ታይተዋል።

በርካታ የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች በግንቦት ወር ለመጨረስ ተቀምጦ የነበረውን የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ ጨርሰዋል።

በመላው ዓለም ተዘጋጅተው የነበሩ ግዙፍ የስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ውድድሮች ቢሰረዙም 44 በመቶ የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች ደግሞ በግላቸው የማራቶን ሩጫን አጠናቀዋል።

ስትራቫ በኦንላየን የእንቅስቃሴ ቡድን መፈጠሩንም አስተውሏል። አባላቱም ቢሆኑ 400 ሚሊዮን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እያደረጉ የተነሷቸውን ምስሎችን አጋርተዋል።

የስትራቫ መስራች ከሆኑት መካከል አንዱ ማይክል ሆርቫት "በዚህ ፈታኝ ዓመት አትሌቶችን ማገናኘት መቻላችንና እንደ ፍላጎታቸው ዓይነት የአካል ብቃት እንዲሰሩ ማነሳሳታችን ደስታን የሚሰጠን ነው- በቨርችዋል ከተደረገ ማራቶን እስከ በእኩለ ቀን ቤት ውስጥ እየሰሩ እስከሚደረግ የእርምጃ እንቅስቃሴ ድረስ።"

አክለውም "በዚህም በመላው ዓለም የሚገኙ አትሌቶች እርስ በእርሳቸው ተሞጋግሰዋል፣ ይህም እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ዋጋ እንዳለው አሳይቷል። እንዲሁም ሰዎች ከእንቅስቀሴ እንዳይርቁ አድርጓል።" ሲሉ ተደምጠዋል።

ሶፊ ፓወር እየሮጠች

የፎቶው ባለመብት, Phil Hill

የ38 ዓመቷ ሶፊ ፓወር ከወረርሽኙ በፊት ዘወትር ሩጫ፣ ብስክሌት መጋለብ ና የቦክስ ግጥሚያ ስፖርት ታዘወትር ነበር።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጣለ በኋላ ግን ነፍሰጡር መሆኗን አወቀች። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሁለት ትንንሽ ልጆች አሏት።

በዚህም የተነሳ ትላለች ሶፊ "ነጻ ጊዜ የሚባለው ነገር በመስኮት ወጥቶ ጠፋ፤ ስለዚህም ሁላችንም በጋራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመርን።" በማለት ከጨቅላ ልጆቿ ጋር ስለጀመረችው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ታስረዳለች።

"ለጥንካሬ በምሰራቸው ስፖርቶች ወቅት በጀርባዬ አዝላቸው ነበር፤ ስትራቫ እጅግ በጣም ሃሪፍ ነው፤ እኔ ስለምጠቀምበት ብቻ ሳይሆን የሚሮጡ ጓደኞቼ በአጠቃላይ የሚሰሩትን ስለማይ ጭምር፤ ያም ከእነርሱ ጋር የበለጠ እንደተቀራረብኩ እንዲሰማኝ አድርጓል። ልክ እንደ አጠቃላይ ሕይወቴ ሁሉ ለኔ በወረርሽኙ ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እጅጉን ወሳኝ ነበር።"

የአእምሮ ጤና

የስፖርት ስነልቦና ባለሙያው ዶ/ር ጂል ኦዌን፣" እርግጠኝነት በጠፋበት እና ቀጣይነት ባልተረጋገጠበት ወቅት፣ ጤና ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሁም ማሕበረሰባዊ በመሆን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሕይወት አዎንታዊ መስመሮች እንዲቀጥሉ ወይንም እንዲፈጠሩ ያደርጋል" ብለዋል።

"መተግበሪያዎች ለተመሳሳይ ዓላማ፣ የጋርዮሽ መደጋገፍን፣ ሃሳብን መለዋወጥ እንዲሁም የአብሮነት ስሜትን መፍጠር ችለዋል።"

"የአእምሮ ጤና በተቃወሰበት ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በማሕበረሰቡ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊደጋገፉ፣ ልምድ ሊለዋወጡ ጤናማ የሆነ የሕይወት መስመር ከመምራት ባሻገር ሊደጋገፉ ይችላሉ" ካሉ በኋላ " የአካልና የአእምሮ ጤና አደጋ ውስጥ በወደቀበት ወቅት፣ ለበርካቶች የማሕበረሰብ ድጋፍ መቀጠል አስፈላጊ ነው" ሲሉ ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።