የግዙፉ መኪና አምራች ግንባታ በእባቦችና በእንሽላሊቶች ምክንያት ተቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግዙፉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መኪናዎች አምራች ኩባንያ ቴስላ በጀርመን ለመገንባት ያሰበው ፋብሪካ በእባቦችና በእንሽላሊቶች ምክንያት ለጊዜው እንዲቆም መገደዱ ተሰምቷል።
የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ በመዲናዋ በርሊን አቅራቢያ በአውሮፓ የመጀመሪያው ነው የተባለውን የመኪና እና የባትሪ ማምረቻ ለመገንባት የደን ምንጣሮ ስራውን በማከናወን ላይ ነበር።
ነገር ግን አንዳንድ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ይህ ምንጣሮ እባብ እና እንሽላሊት ዝርያዎችን ሕልውና አደጋ ላይ ይጥላል በማለት ይከራከራሉ።
ይህን ተከትሎም በፍራንክፈርት የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ምርመራዎች እስከሚከናወኑና ደህንነቱ እስከሚረጋገጥ ድረስ የደን ምንጣሮ ስራው ለጊዜው እንዲቆም ትእዛዝ አስተላልፏል።
ቴስላ እስካሁን በጉዳዩ ላይ በይፋ ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የተፈጥሮ እና ብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ማህበር የሚባል ድርጅት ጋር ከገባበት ክስ ሂደት ጋር እንዳይጋጭበት በማሰብ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።
የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች እንደሚሉት የቴስላ ደን ምንጣሮ ስራ በአሸዋ ውስጥ የሚኖሩ የእንሽላሊት እና እባቦችን ሕይወት በእጅጉ ይጎዳል። እነዚህ ተሳቢ እንስሳት ደግሞ በአገሪቱ ጥበቃ ከሚደረግላቸው እንስሳት መካካል ናቸው ተብሏል።
''ግዙፉ ቴስላም እንኳን ቢሆን እራሱን ከሕግ በላይ ማድረግ አይችልም፤ የለበትምም'' ሲሉ ተደምጠዋል 'ግሪን ሊግ' የተባለው የአካባቢ ጥበቃ ቡድን ዋና ሐሀፊ ሄይንዝ ማስቸር።
የቴስላ መስራችና ዋና ኃላፊ ኤለን መስክ በያዝነው ህዳር ወር መጀመሪያ አካባቢ ድርጅቱ በአውሮፓ የመጀመሪያውን ፋብሪካ ግንባታ ሊያካሂድ መሆኑን ይፋ ሲያደርጉ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2021 ላይ ወደ ስራ ለመግባት መታቀዱን ገልጸው ነበር።
በዓመትም 500 ሺ መኪኖችን ለማምረት እቅድ ተይዞ ነበር።
ኃላፊው አክለውም ቴስላ ጀርመን ውስጥ ከመኪና ማምረቻው ጎን ለጎን በዓለማችን ትልቁ የሆነ የመኪና ባትሪ ፋብሪካ ለመገንባት መታቀዱን ኤለን መስክ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
ነገር ግን ግንባታው የሚካድሄበት አካባቢ የግንባታው ሂደት በአካባቢ ተቆርቀቋሪዎችና ግንባታው ለጀርመን የወደፊት የንግድ እንቅስቃሴ ትልቅ ፋይዳ አለው በሚሉ ቡድኖች መካከል ጭቅጭቅን አስነስቷል።
ምንም እንኳን የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቴስላ ግንባታውን እንዲጀምር ፈቃድ ቢሰጠውም ግንባታው በሚካሄድበት አካባቢ የሚገኙ ኃላፊዎችን ይሁንታ ማግኘት ግን የቴስላ ነው።
የአካባቢው ባለስልጣናት ደግሞ ነዋሪዎችንና የአካባቢ ተቆርቋሪዎችን አስተያየትና ግምገማ ከተቀበሉ በኋላ ነው የግንባታ ፈቃድ የሚሰጡት።
ከዚህ በተጨማሪ ምንጣሮው የሚካሄድበት አካባቢ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተቀብረው የነበሩ ሰባት ቦምቦች መገኘታቸው ደግሞ ለቴስላ ነገሮችን ይበልጥ አስቸጋሪ አድርጎታል።












