ኮሮናቫይረስ፡ ጆ ባይደን በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት 100 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ አቅጃለሁ አሉ

ታትሟል

አዲሱ የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን በመጡ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት 100 ሚሊዮን ሰዎች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እንዲያገኙ ለማድረግ ግብ አስቀምጠው እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

ባይደን አክለውም ምንም እንኳን በመጀመሪያዎቹ የስልጣናቸው ወራት ወረርሽኙን ማጥፋት ከባድ እንደሚሆን ባይክዱም ክትባቱ እንዴት እንደሚከፋፈልና ጉዳቱ እንዴት መቀነስ እንደሚቻል ግን እቅድ አዘጋጅተናል ብለዋል።

ተመራጭ ፕሬዝዳንቱ ጥር ወር ላይ ስራ የሚጀምረው የጤና ቡድናቸውን በሚያስተዋውቁበት ሰአትም አሜሪካውያን ለመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ትናንት ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ፋይዘር/ባዮንቴክ የሚያመርተው ክትባት ለአሜሪካውያን መከፋፈል እንዲጀመር የሚረዳ አንድ ሪፖርት መውጣቱ ደግሞ በበርካቶች ዘንድ ተስፋን አጭሯል።

በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮቪድ ክትባት ፕሮግራማቸውን በተመለከተ ዋይት ሀውስ ውስጥ ስብሰባ ያካሄዱ ሲሆን በቅርቡ ፈቃድ ይሰጠዋል የተባለውን ክትባት ፍጥነት አድንቀዋል ተብሏል።

በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ መሰረት አሜሪካ እስካሁን ድረስ 15 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮረናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 285 ሺ ሰዎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ይህ ቁጥር በአለማችን ከፍተኛው ነው።

በአሁኑ ሰአት በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች እንደ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም ወደ ሆስፒታሎች እየገቡ ስለመሆናቸው ተዘግቧል።

ባይደን ምን አሉ?

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዴልዌር ውስጥ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ''በእኔ የመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት የኮቪድ-19 ቫይረስን ማጥፋት አይቻልም። ይህንን ቃል መግባት አልችልም። ወደዚህ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዳለመግባታችን ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው'' ብለዋል።

አክለውም ''በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት የቫይረሱን ስርጭትና አካሄድ በእጅጉ መቀየር እንችላለን፤ በዛውም የአሜሪካውያንን ሕይወት መቀየር እንችላለን'' ሲሉ ተደምጠዋል።

ነገር ግን ጆ ባይደን የአሜሪካ ኮንግረስ በፍጥነት ለክትባቱና መከላከል ስራዎች የሚሆን ገንዘብ በፍጥነት የማያጸድቅ ከሆነ ''ጥረታችን ሊንቀራፈፍ ይችላል'' ብለዋል።

ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት መመለስም ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ተመራጩ ፕሬዝዳንት አስምረዋል።

ባይደን ምናልባትም በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ ሊሆን የሚሆነውን የክትባት ዘመቻ እንዴት ለማከናወን እንዳሰቡ ግን ዝርዝር መረጃ ከመስጠጠት ተቆጥበዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዋይት ሀውስ በነበረው ስብሰባ ላይ ክትባቱ በቅርቡ ፈቃድ እንደሚያገኝ ተስፋቸውን ገልጸዋል። ''አንዳንዶች ይህ ተአምር ነው ይላሉ፤ እውነቱን ለመናገር እኔም እንደዛ ነው የማስበው'' ብለዋል።

አክለውም ''ክትባቱን ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም አሜሪካዊ ክትባቱ እንዲያገኝ ይደረጋል፤ በሚቀጥሉት ወራትም ማንም እንደርስበታለን ብሎ ካልገመተው ቦታ እንደርሳለን'' ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር እስከ ፈረንጆቹ ጥር ወር አጋማሽ ድረስ ብቻ 24 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ አቅዶ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።