አሜሪካ በአንድ የጦር ሰፈር ውስጥ ሞተው የተገኙ ወታደሮች ላይ ምርመራ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ በአንድ የጦር ሰፈር ውስጥ ሞተው የተገኙ ሁለት ወታደሮችና አንድ የቀድሞ የጦር መኮንን ሞት እያጣራሁ ነው ብላለች።
ወታደሮቹ ተገድለው ሊሆን ይችላል የሚሉ ጥርጣሬዎችም ወጥተዋል።
ዊልያም ጄ ላቪጅንና ቲሞቲ ዱማስ አስከሬን የተገኘው ሰሜን ካሮላይና ውስጥ የሚገኝ ፎርት ብራግ የተባለ የጦር ሰፈር ውስጥ በዚህ ሳምንት ረቡዕ እለት ነው።
ባለስልጣናቱ ወታደሮቹ የሞቱት ከስልጠና ጋር በተያያዘ አይደለም ብለዋል።
ፎርት ብራግ በአለም ላይ ካሉ ትልቁ የጦር ሰፈር ሲሆን፣ 57 ሺህ በስራ ላይ ያሉ ወታደሮችና የጦር መኮንኖች መቀመጫ ነው።
የአሜሪካ ሰራዊት ልዩ የተልዕኮ ኮማንድ እንዳስታወቀው የ37 አመቱ ዊልያም በአፍጋኒስታንና ኢራቅ በተደጋጋሚ ተመድቦ የተዋጋ ሲሆን በጦሩም ውስጥ ለ19 አመታት ቆይቷል።
የ44 አመቱ ቲሞቲ ዱማስ ከጎሮጎሳውያኑ 1996-2016 ድረስ በጦሩ እንዳገለገለ አንድ የፔንታጎን ጦሩ ቃለ አቀባይ ስታርስ ኤንድ ስትሪፕስ ለተባለ ወታደራዊ ጋዜጣ ተናግረዋል።
የወታደሮቹ አስከሬን በጦር ሰፈሩ ማሰልጠኛ ቦታ ነው የተገኘው። በቦታውም ምንም አይነት የጦር መሳሪያም እንዳልተገኘው አንድ የጦር ባለስልጣን ለአሜሪካ ሚዲያዎች ተናግረዋል።
ሆኖም አስከሬናቸው በተገኘበት አካባቢ የጥይት ባሩዶች መገኘታቸውን የጦር ባለስልጣኑ ለቢቢሲ ዩኤስ አጋር ሲቢኤስ የዜና ወኪል ገልፀዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አንድ ኃላፊ ለአሜሪካ ሚዲያዎች እንደተናገሩት ሁለቱም ወታደሮች አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀምና በመሸጥ ተጠርጥረው እየተመረመሩ እንደነበር ነው።
የአሜሪካ የጦር ወንጀል ምርመራ ዕዝም በወታደሮቹ ላይ የሚደረገውን ምርመራ በዋነኝነት እየመራ ይገኛል።
ከዚህ ቀደምም ኤንሪክ ሮማን ማርቲኔዝ የተባለ ወታደር በዚሁ የጦር ሰፈር መሞቱ ከታወቀ በኋላም ምርመራ እየተከናወነ ነው።
ሮማን ማርቲኔዝ ከሰባት ወታደሮች ጋር አብረው የእግር ጉዞ ለማድረግ እንደወጡ በዚያው የጠፋው ግንቦት ወር ላይ ነበር። ከቀናት በኋላም የተወሰነው የአስከሬኑ ክፍል በሃይቅ ዳርቻ ተገኝቷል።












