ትራምፕ የአንድ ግዛት አስተዳዳሪ የምርጫ ውጤት እንዲቀይሩ እየወተወቱ ነው

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሪፐብሊካኑ የጆርጂያ ግዛት አስተዳዳሪ የጆ ባይደንን ድል እንዲቀለብሱላቸው ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።

ፕሬዝደንቱ አከታትለው የትዊተር ግድግዳቸው ላይ በለጠፏቸው መልዕክቶች የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ብራያን ኬምፕ ውጤቱን እንዲቀለብሱ ወትውተዋል።

ትራምፕ ጆርጂያ ተገኝተው በቅርቡ ለሚካሄደው የላይኛው ምክር ቤት እንደራሴዎች ምርጫ ቅስቀሳ አካሂደዋል።

የአሜሪካ ምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነ ቢቆይም ትራምፕ ግን ውጤቱን አምነው አልተቀበሉም።

አልፎም ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል ማስረጃ የሌለው ዜና እያወጁ ይገኛሉ።

ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ውጤቱን ለመቀልበስ ክስ ቢመሰርቱም አልተሳካላቸውም።

ጆርጂያ በዘንድሮው ምርጫ እጅግ ወሳኝ ሚና ከተጫወቱ ግዛቶች መካከል ናት።

ጆ ባይደን በጠባብ ውጤት ነው ትራምፕን በጆርጂያ የረቱት። በፈረንጆቹ ከ1992 በኋላ በዚህች ግዛት ያሸነፉ የመጀመሪያው የዴሞክራት ፓርቲ ዕጩም ሆነዋል።

በቅርቡ ደግሞ የላይኛው ምክር ቤት እንደራሴዎች ምርጫ ይከናወንባታል።

በዚህች ግዛት የዴሞክራት ፓርቲ ዕጩዎች ምርጫውን ማሸነፍ ከቻሉ ሪፐብሊካኖች በምክር ቤቱ ያላቸውን የበላይነት ያጣሉ።

እንደ ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ከሆነ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ሃገረ ገዠ ኬምፕ ጋር ደውለው የምርጫው ውጤት ድጋሚ እንዲጣራ ጠይቅ ሲሉ ወትውተዋል።

ይህን የማድረግ ሥልጣን ያላቸው ሃገረ ግዥ ኬምፕ ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ይላል የጋዜጣው ዘገባ።

ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫ ሰዎች በፖስታ መምረጣቸው ምርጫው እንዲጭበረበር አስተዋፅዖ አድርጓል ይላሉ። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ አልተገኘም።

ትራምፕ በጆርጂያ ሁለት ሰዓት የፈጀ ንግግር አድርገዋል።

ምንም እንኳ ግዛቲቱ የሄዱት ለምክር ቤት አባላት ዕጩዎች ለመቀስቀስ ቢሆንም ምርጫው ባይጭረበረበር እሳቸው በቀላሉ እንደሚረቱ ያልተረጋገጠ ወሬ ሲነዙ አምሽተዋል።

ደጋፊዎቻቸውም የሳቸውን ወቀሳ ተከትሎ 'ማጭበርበሩ ይብቃ' የሚል ጩኸት ሲያሰሙ አምሽተዋል።

ዴሞክራቱ ጆ ባይደን የአሜሪካን ምርጫ ማሸነፋቸው ታውጇል። በቀጣይ ጥር ምክትላቸው ከማላ ሃሪስን ይዘው ወደ ዋይት ኃውስ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።