በአሻንጉሊቶች ውስጥ የተሰፉ ብርቅዬ እንስሳት ወደ ጀርመን ሊገቡ ሲሉ ተያዙ

ከዳኑት እንሽላሊት መካከል

የፎቶው ባለመብት, Presseportal.de

ታትሟል

የጀርመን አየር ማረፊያ የጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች ከሰሞኑ 26 ብርቅዬ ተሳቢ እንስሳት በሕገወጥ መንገድ ሊያልፉ ሲሉ ይዘዋል።

እንስሳቶቹ ከሜክሲኮ በአሻንጉሊቶችና በጣፋጮች ውስጥ ታሽገው ነው በድብቅ ጀርመን የደረሱት። ከእነዚህም ውስጥ አስሩ ሞተዋል።

የተወሰኑት ተሳቢ እንስሳቶች ከልብስ በተሰሩ አሻንጉሊቶችም ተሰፍተው የነበረ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት ታፍነው እንደሞቱ ከኮሎኝ ቦን አየር ማረፊያ ጉምሩክ ቢሮ የወጣው መግለጫ ያስረዳል።

እነዚህ ለአደጋ የተጋለጡት ተሳቢ እንስሳትም መካከል ብርቅዬ የሆኑ ቀንድ ያላቸው አንሽላሊት፣ የአዞ ዝርያ ያላቸው እንሽላሊት፣ እንዲሁም ለየት ያሉ ኤሊዎች ነበሩበት።

እነዚህን እንስሳትም ጀርመን ውስጥ ለሚገኝ አንድ ገዢ ለማድረስም ታቅዶ ነበር።

እነዚህ ተሳቢ እንስሳት ብርቅዬ ከመሆናቸውም ጋር ተያይዞ ዓለም አለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሊጠብቃቸው ይገባልም ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ይገኙበታል።

በአሻንጉሊት የተሰፉት እንስሳት

የፎቶው ባለመብት, Presseportal.de

የጀርመን ባለስልጣናት የእንስሳቶቹን ዘረመል በመጠቀም ከየት እንደመጡም ለማወቅም ምርመራ ጀምረዋል።

እንስሳቶቹን ለማራባት ካሉ የቤተ ሙከራ ፕሮግራሞች ወይስ ከዱር ተይዘው ነው እዚህ የደረሱትም የሚለውንም እንደሚያጣሩ አሳውቀዋል።

እንስሳቱ በሁለት ጥቅሎች ታሽገው በሳምንት ልዩነት ነው ጀርመን አየር ማረፊያ የገቡት።

የጉምሩክ ቢሮ፣ ከሜክሲኮ ባለስልጣናትና በቦን የሚገኘው የእንስሳት ምርምር ተቋም፣ አሌክሳንደር ኮይንግ ሪሰርች ሙዝየም ጋር ተባብረው እየሰሩ ነው።

ፖሊስ እስካሁን ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹን ያላገኘ ሲሆን ከተገኙም ቅጣት ይደርስባቸዋል ተብሏል።

በህይወት ያሉት 16ቱን እንስሳትም ለሜክሲኮ ለመመለስ እቅድ ተይዟል።

አደጋ ላይ ያሉና ብርቅዬ የሆኑ እንስሳትን ጥበቃ በተመለከተ ዓለም አቀፍ ድንጋጌ ያለ ሲሆን፤ የአውሮፓ ኅብረትና 182 አገራት ተቀባይነት በማግኘትም ፈርመውበታል።

ድንጋጌውም 6 ሺህ የእንስሳት አይነቶችንና 30 ሺህ የእፅዋት አይነቶችን ያካተተ ነው።