በአሻንጉሊት ታሽገው ወደ ጀርመን የገቡት የሜክሲኮ እንሽላሊቶች

በአሻንጉሊት ታሽገው ወደ ጀርመን የገቡት የሜክሲኮ እንሽላሊቶች

የፎቶው ባለመብት, PRESSEPORTAL.DE

ታትሟል

የጀርመን አየር ማረፊያ ገቢዎች ባለሥልጣን 26 ተሳቢ እንስሳት የአሻንጉሊት ለምድ ለብሰው ወደ ሃገር ቤት ሊገቡ ሲሉ ይዣቸዋለሁ ብሏል።

በአሻንጉሊትና ጣፋጭ ከረሜላ መሸፈኛዎች ታሽገው ከሜክሲኮ ወደ ጀርመን ከተጋዙት ተሳቢ እንስሳት መካከል አስሩ ሞተዋል ተብሏል።

ከተሳቢ እንሳስቱ መካከል አደጋ ላይ ያሉ የእንሻላሊት ዝርያዎች፤ ትናንሽ አዞዎች እንዲሁም የኤሊ ዝርያዎች ይገኙባቸዋል ተብሏል።

ተሳቢ እንስሳቱ ጀርመን ላሉ ገዢዎች የታለሙ ነበሩ።

በዓለም ዙሪያ በርካታ አደጋ ላይ ያሉ እንስሳት በድብቅ ከሃገር ሃገር ይዘዋወራሉ።

የጀርመን ባለሥልጣናት ከተሳቢ እንሰሳቱ ላይ ዘረ መል መዘው ከየት እንደመጡ ለመለየት እየጣሩ ይገኛሉ።

እንሰሳቱ ከዱር የተገኙ ይሁኑ አሊያም ከግል የእንስሳት ማቆያዎች እስካሁን ማወቅ አልተቻለም።

እንሳስቱ በሁለት ሳጥኖች ታሽገው ሲመጡ ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

የጀርመን ገቢዎች ባለሥልጣን ከሜክሲኮ ባለሥልናት ጋር ተባብሮ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹን ለመያዝ እየጣረ ይገኛል።

ፖሊስ አዘዋዋሪዎቹን ካገኘ ከባድ ቅጣት ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

አስራ ስድስቱ በሕይወት የተረፉት ተሳቢ እንስሳት ወደ ሜክሲኮ ተመልሰው ከተሳቢ ዘመዶቻቸው ጋር ይቀላሉ ተብሏል።

በፈረንጆቹ 1973 የተፈረመ አንድ ስምምነት በ182 የዓለማችን ሃገራት ይሁንታ አግኝቷል።

ኢትዮጵያም የዚህ ስምምነት አባል ናት። የአውሮፓ ሕብረትም ይህን ስምምነት ፈርሟል።

በስምምነቱ ላይ እንደተቀመጠው 6 ሺህ ዓይነት ተሳቢ እንስሳትና 30 ሺህ ዕፅዋት ማዘዋወር በሕግ ያስቀጣል።