ኮሮናቫይረስ፡ ባንግላዴሽ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሮሂንጃ ስደተኞች ከመጠለያ ጣቢያቸው እንዳይወጡ አገደች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባንግላዴሽ ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሮሂንጃ ስደተኞች ከመጠለያ ጣቢያቸው መውጣትም ሆነ መግባት አይችሉም በሚል ውሳኔ አስተላልፋለች።
በደቡባዊ ግዛቷ የሚገኘውን የመጠለያ ጣቢያ የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለችው ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መዛመትን ፍራቻ እንደሆነ አሳውቃለች።
ስደተኞች ከጣቢያቸው እንዳይንቀሳቀሱ ከማገድ በተጨማሪ ከውጭ ለሚመጡ ጎብኝዎችም መግባት የተከለከለ ነው ተብሏል።
በመጠለያ ጣቢያው እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ባይኖርም የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች ወረርሽኙ ቢነሳ ካለው ዝቅተኛ የህክምና ሽፋን ጋር ተደራርቦ ችግሩን ሊያከፋው እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።
የግዛቷ አስተዳዳሪ ከማል ሁሴን ይህ እርምጃ የተወሰደው በአገሪቷ ውስጥ እተከሰተ ያለው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ነው ብለዋል።
በባለፉት አምስት ቀናት ቁጥሩ በእጥፍ ያደገ ሲሆን እስካሁንም ባለው መረጃ 200 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፤ 20 ግለሰቦችም ህይወታቸውን አጥተዋል።
ይህንንም ተከትሎ በግዛቷ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ የተከለከለ ሲሆን ይህንንም ተላልፎ የተገኘ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠበቀው አስጠንቅቀዋል።
በተለይም ለመጠለያ ጣቢያው ይህ ሁኔታ የከፋ ሲሆን የእርዳታ ሰራተኞች እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
ድንገተኛ ምግብና ከህክምና ቁሳቁሶች በስተቀር መግባት እንደማይቻል የስደተኞች ኮሚሽነሩ ማህቡብ አላም ታሉክደር ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል አሳውቀዋል።
ፖሊስና ወታደሮች በግዛቷ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ድንጋይ በማስቀመጥ እየተከላከሉ ሲሆን መጠለያ ጣቢያውም በወታደሮች እየተጠበቀ ነው።
በርካታ ቁጥር ያላቸው የሮሂንጃ ስደተኞች ከሶስት አመታት በፊት ማይናማር ውስጥ የተከሰተውን ጭፍጨፋ ፍራቻ ነው ወደ ባንግላዴሽ የደረሱት።
ከ750 ሺ የሚበልጡ ስደተኞች ድንበር አቋርጠው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደሚኖሩበት መጠለያም አቅንተው ተቀላቅለዋቸዋል።














