ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡አወዛጋቢው የትራምፕ የኮሮናቫይረስ ልዩ አማካሪ ሥልጣን ለቀቁ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ልዪ አማካሪ የነበሩት ዶክተር ስኮት አትላስ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን ለቀቁ።
"ፕሬዝዳንቱ ሕዝቤን እንዳገለግል ስለፈቀዱልኝ አመግናለሁ፥ ሁልጊዜም ከፖለቲካ ሳይሆን ከሳይንስ ጋር ነው የወገንኩት" ብለዋል በመልቀቂያ ማስታወሻቸው ላይ።
ዶ/ር አትላስ ኮሮናቫይረስን እንዲከላከል ከተቋቋመው ግብረኃይል ጋር በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ የገቡ የጤና ባለሞያ ናቸው።
ራዲዮሎጂስትና የሳንፈርድ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የነበሩት ዶ/ር አትላስ የኮሮና ግብረኃይሉን የተቀላቀሉት ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ ነበር።
የጭምብል አስፈላጊነት በማራከሳቸው ከትራምፕ የሚወግኑ ሰው ናቸው በሚል በሚዲያ የሚብጠለጠሉ ሰው ነበሩ።
ሥርጭቱን ለመግታት ከተሞችን መዝጋት አስፈላጊ አይደለም የሚል አቋም በማራመዳቸውም ብዙዎች ይወቅሷቸዋል።
የጋርዮሽ የበሽታ መከላከል አቅምን መፍጠር (Herd Immunity) ተህዋሲውን ለማጥፋት ምርጡ መንገድ ነው ብለው መከራከራቸው ዶ/ር አትላስን ልዩ ያደርጋቸዋል።
የኅብረተሰብ ጤና ሊቅ ደ/ር አንተኒ ፋውቺ እና የአሜሪካ የመድኃኒትና ተዛማች በሽታዎች መቆጣጠርያ ማዕከል (ሲዲሲ) እኚህን ሥልጣን የለቀቁትን ከፍተኛ አማካሪ ክፉኛ ይተቿቸዋል።
ለዶናልድ ትራምፕ የማይሆን ምክር እየሰጡ ብዙ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብለውም ይታማሉ።
ከርሳቸው ጋር በዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ ባልደረቦቻቸው ሳይቀር ሳይንስ ተምረው ሳይንስን የሚቃረኑ ዶ/ር ሲሉ ነው የሚተቿቸው።
ሰውየው ሥልጣን ለመልቀቅ እንዲያውም ዘግይተዋል፤ በሐሰተኛ መረጃና ሳይንስን ቸል በማለት ብዙ ጉዳት አድርሰዋል ይላሉ ባልደረቦቻቸው።
ዶናልድ ትራምፕ ይህንን ተህዋሲ በራሱ ጊዜ የሚጠፋ ተራ ጉንፋን ነው በሚል ሲያቃልሉት ቆይተዋል።
ሆኖም ሕዝባቸው ላይ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊና የጤና ቀውስ ከማምጣቱም ባሻገር እርሳቸውም ከነጩ ቤተመንግሥት እንዲወጡ ጦስ ሳይሆንባቸው አልቀረም።
መጪው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጭምብል ማጥለቅ ላይ ጥብቅ እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት አላቸው።
የተያዙ ሰዎችን በመከታተል ሥርጭቱን ለመግታትም ቆርጠው መነሳታቸውን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሲያወሱ ነበር።
አሜሪካ በተህዋሲው 13 ሚሊዯን ዜጎች ተይዘውባታል። 266ሺህ አሜሪካዊያን ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ይህ አሐዝ ባለፈው ሳምንት በተከበረው "ታንክስ ጊቪንግ" ምክንያት ከፍተኛ ማሻቀብ እንደሚያሳይ ዶ/ር ፋውቺ ተናግረዋል።