ፌስቡክ በአዲሱ ዓመት ለዜና አውታሮች ክፍያ ሊጀምር ነው

የፌስቡክ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ፌስቡክ በአዲሱ ዓመት ታላቋ ብሪታኒያ ውስጥ ለሚገኙ ዜና ሰሪ አውታሮች ክፍያ መክፈል ሊጀምር ነው።

ለዚህም የፌስቡክ መተግበሪያው ላይ ራሱን የቻለ የዜና መጠቆምያ ነቁጥ ይበጅለታል ተብሏል።

ይህ አገልግሎቱን በአሜሪካ ከወዲሁ ሥራ ጀምሯል ተብሏል። በታላቋ ብሪታኒያ ደግሞ ከአንድ ወር በኋላ በአዲሱ ዓመት ይጀምራል።

ፌስቡክ ክፍያ የምፈጽምላቸው የዜና አገልግሎቶች ዜናውን በራሳቸው ገጽ ያላተሙ ከሆነ ብቻ ነው ብሏል።

ይህም ማለት የዜና አገልግሎቶቹ በፌስቡክ እንዲከፈላቸው ከፈለጉ ዜናውን ለፌስቡክ ብቻ የሚጽፉት ይሆናል። በራሳቸው ድረገጽም ሆነ በጋዜጦቻቸው ላይ ሊያትሙትም አይችሉም።

ፌስቡክ ላይ እንጂ የትም ላልታተሙና የይዘት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ናቸው ለሚባሉ የዜና ዘገባዎች ብቻ ክፍያ እፈጽማለሁ የሚለው ድርጅቱ የዜና ዘገባዎችንና ስርጭትን ያለምንም ክፍያ ለደንበኞቹ ሲያጋራና ሲጠቀምበት ነበር፥ በዝባዥ ሆኖ ቆይቷል በሚል ሲተች ነበር።

የዜና አገልግሎት ሰጪ አውታሮች፣ የሚዲያ ይዘት አታሚዎችና አሰራጮች ከፌስቡክ ጋር ለረዥም ጊዜ ሲካሰሱ ቆይተዋል።

ዜና አገልግሎቶች ፌስቡክ እኛ የለፋንበትን ቱባ ዜና አንዳችም ክፍያ ሳይፈጽም ለደንበኞቹ ማጋራቱ ስግብግብነቱን ያሳያል ሲሉ ይወቅሱታል።

አሁን በታላቋ ብሪታኒያ በመቶዎች የሚቆጠሩ መገናኛ ብዙኃን ከፌስቡክ ጋር በጥምረት ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ከፌስቡክ ጋር ስምምነት ከፈጸሙ አሳታሚዎች መሀል ሄርስት፣ ዘ ጋርዲያን ሚዲያ ግሮፕ፣ ጄፒአይ ሚዲያ እና ሚድላንድ ኒውስ አሶሲየሽን ይገኙበታል።

ፌስቡክ ቀሪዎቹ የዜናና ሌሎች የሚዲያ ይዘት አሳታሚዎች የፌስቡክ ዜና አገልግሎቱ ከተጀመረ በኋላ ስምምነት ይፈጽማሉ ሲል አስታውቋል።

ያም ሆኖ ፌስቡክ መተግበሪያ ላይ የዜና ገጽ መጠቆሚያዋ የምትገኘው በሞባይል የፌስቡክ መተግበሪያ ላይ ብቻ ይሆናል።

አንድ ደንበኛ በኮምፒውተር የድረ ገጽ ማሰሻ ላይ ፌስቡክ ገጽ ቢከፈት የዜና ማንበቢያ የሆነችውን ነቁጥ አያገኛትም።

ፌስቡክ አገልግሎቱን በአሜሪካ ከጀመርኩ ጀምሮ የዜና አገልግሎቶቹን ከዚያ በፊት አንብበዋቸው የማያውቁ 95 ከመቶ ደንበⶉቼ ዜና ማየት ጀምረዋል ብሏል።

ይህ ምናልባት ፌስቡክ ከመጣ ወዲህ በከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል ለሚባሉት ዜና አገልግሎቶች ሰጪዎች አዲስ ተስፋን የሰነቀ ሆኗል።

ዜና አታሚዎች በፌስቡክ በኩል ዜናዎቻቸው ለአንባቢ መድረሱ ይበልጥ እንዲታወቁ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ተስፋ አለ።

ፌስቡክ ከነዚህ ሚዲያዎች ጋር ያደረገው ስምምነት ይዘት ምስጢር ሆኖ ተቀምጧል።

ስለዚህ ዜና አገልግሎቶቹ ከፌስቡክ ጋር በመቀናጀታቸው የሚያገኙት ክፍያ ምን ያህል ሊሆን ይችላል የሚለውን ማወቅ አልተቻለም።

ቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ በባለቤትነት የሚያስተዳድሯቸው ግዙፍ ሚዲያዎች የሚሰሯቸው ዜናዎችና ሌሎች ይዘቶች በፌስቡክ እየተዘረፉብን ነው፤ ስለዚህ ትልልቅ ኩባንያዎች ለዜና አገልግሎቶች ተገቢ ክፍያ መፈጸም አለባቸው በማለት ሲሟገቱ ኖረዋል።

በዓለም ላይ እጅግ አትራፊ ናቸው የሚባሉትና ሀብታቸው ያለ ተቀናቃኝ አለቅጥ እያበጠና እየተለጠጠ የሚገኙት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሕዝብን ለሚጠቅሙና በጠራ መረጃ የበለጸገ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ለሚያግዙ የዜና አውታሮች ትርፍ ማጋራት አለባቸው የሚለው ክርክር በርካታ ዘመን ያስቆጠረ ነው።

በተጠቃሚዎች ዘንድም ቢሆን የደረጀና የጠራ መረጃን ከማግኘት ይልቅ ግልብና ሐሳዊ መረጃ ወደሚራገብባቸው የማህበራዊ ድረገጾች ይበልጥ የመሳብ ዝንባሌ እውቅ ዜና አውታሮችን ሳይቀር ከገበያ እያስወጣቸው ነበር።

በዓለም ላይ ከመቶ ዓመታት በላይ ሲታተሙ የቆዩ ጋዜጦች ሳይቀር በገቢ መቀጨጭ ከገበያ መውጣታቸው ይታወቃል።