የታይዋን ፓርላማ አባላት የአሳማ ስጋ በመወርወር ተቃውሟቸውን ገለፁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የታይዋን የተቃዋሚ ፓርላማ አባላት የአሳማ ስጋ በመወርወርና በቡጢም በመደባደብ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።
ከአሜሪካ የሚገባው የአሳማ ስጋ ምርት ጋር የተያያዘው መመሪያ ቀለል ብሏል በሚልም ነው ፓርላማው ውስጥ ይህ የተፈጠረው።
በቅርቡም የታይዋን መንግሥት ከአሜሪካ እንዲገባ የፈቀደው የአሳማ ስጋ ራክቶፓሚን የሚባል ሱስ የሚያስይዝና በታይዋንና በአውሮፓ ህብረት የታገደ ንጥረ ነገር የያዘ ነው ተብሏል። ንጥረ ነገሩ ለጤና ስጋትም እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ታይዋንም ለአሳማ ስጋዎች ጥቅም ላይ እንዳይውል ከልክላዋለች።
ገዢው ፓርቲው በበኩሉ ይህን ክስ ያስተባበለ ሲሆን ምክንያታዊ ወደሆኑ ንግግሮችም እንዲመለሱ ጠይቋል።
እንዲህ አይነት ቁጣዎችና ድብድቦች ለታይዋን ፓርላማ አዲስ አይደሉም።
የታይዋን ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ኩዎሚንታ (ኬኤምቲ) ፓርቲ የአሳማ አንጀትና ስጋ በባልዲ ይዘው ወደ ፓርላማ በማምጣትና በመወርወር ጠቅላይ ሚኒስትር ሱ ሴንግ ቻንግ ጥያቄና መልስ እንዳያካሂዱም ለማድረግ ሞክረዋል።
የአሳማ አንጀት መወርወር ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚው ፓርቲ ኬኤምቲና ቼን ፖ ዌይ በተባለው ፓርቲ አባላት መካከልም ቡጢ እንደተሰነዘረም ሮይተርስ የዜና ወኪል አስነብቧል።
ገዢው ዲሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ "አፀያፊ ተቃውሞ" በሚል ያወገዘው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ምግብ መባከኑና ፓርላማውም በመጥፎ ጠረን መታወዱን የማይገባ ተግባር ነው ብሎታል ። ፓርላማው ወደ ምክንያታዊ ክርክር እንዲገባም ጥያቄ ቀርቧል።
የታይዋን ፕሬዚዳንት ትሳይ ኢንግ ከአሜሪካ የሚገባውን የአሳማ ስጋ ምርት በማስመልከት የተጣለውን መመሪያ ያቀለሉት ነሐሴ ወር ላይ ሲሆን፤ ከጥር ጀምሮም ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል። ውሳኔው አሜሪካን ሲያስደስት የታይዋን ተቃዋሚዎች ግን ህዝቡ ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን የጤና እክል በማንሳት ተግባራዊ እንዳይሆን ይሞግታሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከዚህ ቀደምም በርካታ ሰልፈኞች ተቃውሟቸውን ገልፀው ነበር።
ሱስ ያስይዛል የሚባለው ራክቶማፖን በታይዋል፣ በቻይናና በአውሮፓ ህብረት አባል አገራት ለሰው ልጅና ለእንስሳት ከሚያስከትለው የጤና ስጋት ጋር ተያይዞም እግድ ተጥሎበታል።
ዩዋን የተባለው የታይዋን ፓርላማ ቡጢ መሰነዛዘር፣ ፀጉር መጎተት፣ የውሃ ፕላስቲክ መወርወርንም በአመታት ውስጥ አስተናግዷል።
በተለይም ከሶስት አመት በፊት የመሰረተ ልማት ፍሰት ላይ በተነሳ ክርክር የፓርላማ አባላቱ ወንበር አንስተው ሲወራወሩ ነበር።












