በአፍጋኒስታን ጦርነት 26 ሺህ ህጻናት ተገድለዋል አልያም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተባለ

የአፍጋኒስታን ህጻናት
ታትሟል

በጦርነት በምትታመሰው አፍጋኒስታን ላለፉት 14 ዓመታት በአማካይ በየቀኑ አምስት ህጻናት እንደተገደሉ ሴቭ ዘ ቺልድረን የተባለው የተራድኦ ድርጅት አስታወቀ።

ከተባበሩት መንግሥታት በተገኘ መረጃ መሰረት ደግሞ ከአውሮፓውያኑ 2005 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ቢያንስ 26 ሺህ 025 ህጻናት በጦርነቱ ምክንያት ተገድለዋል፣ ቆስለዋል አልያም ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል ድርጅቱ።

ሕጻናት አድን ድርጅቱ (ሴቭ ዘ ቺልድረን) የሕጻናትን የወደፊት እጣ ፈንታ ለማስተካከልና ሕይወታቸውን ለማቃናት ለጋሽ አገራት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪውን አስተላልፏል።

በአፍጋኒስታን ምንም እንኳን የሰላም ስምምነቶች በተደጋጋሚ ቢደረሱም ተፈጻሚ ባለመሆናቸው ምክንያት የሰዎች ግድያ ጨምሯል፤ የአሜሪካ ወታደሮች መውጣት ደግሞ ነገሮችን ይበልጥ የከፋ አድርጎታል።

አፍጋኒስታን በዓለም ለህጻናት በእጅጉ አደገኛ ናቸው ተብለው ከተፈረጁ 11 አገራት መካከል አንዷ ስትሆን እስካሁንም በርካታ ህጻናት መገደላቸውን ሴቭ ዘ ቺልድረን ጠቁሟል።

ድርጅቱ እንዳስታወቀው በ2019 ብቻ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ 874 ህጻናት የተገደሉ ሲሆን 2 ሺህ 275 ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል አልያም ቋሚ የአካል ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

ሕጻናት አድን ድርጅቱ በሪፖርቱ ላይ ትምህርት ቤቶች በተደጋጋሚ የጥቃት ሰለባ እንደሚሆኑ የገለጸ ሲሆን ጥቃቶቹ የሚፈጸሙት በአሜሪካ ወታደሮች በሚደገፈው መንግሥትና ታሊባን እንዲሁም ሌሎች ታጣቂዎች መካከል በሚደረጉ ጦርነቶች ነው ብሏል።

አክሎም ከአውሮፓውያኑ 2017 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ብቻ ከ300 በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።

''እስቲ አስቡት፤ ማቆሚያ በሌለው የጦርነት ቀጠና ውስጥ ትምህርት ቤት ልጆችን መላክ። ወላጆች ዛሬ ልጄ ይሞትብኝ ይሆን እያሉ ይጨነቃሉ። ይህ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ቤተሰቦችና ህጻናት እውነታ ነው'' ብለዋል የሴቭ ዘ ቺልድረን የአፍጋኒስታን ዳይሬክተሩ ክሪስ ንያማንዲ።