መካከለኛው ምሥራቅ ፡ ሳዑዲ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር 'ምስጢራዊ ውይይት' ተደርጓል መባሉን አስተባበለች

ታትሟል

የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከልዑሉ ጋር ምስጢራዊ ውይይት ለማድረግ ወደ ሳዑዲ ተጉዘዋል መባሉን አስተባበለ።

"እንዲህ አይነት ግንኙነት ፈጽሞ አልተደረገም" ሲሉም ሚኒስትሩ ልዑል ፋይሳል ቢን ፋርሃን አል ሳዑድ ትዊተር ላይ አስፍረዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማንና ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮን ጋር ለመነጋገር እሁድ በሚስጥር ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማቅናታቸውን የዘገቡት የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ናቸው።

የበረራ መከታተያ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኔታንያሁ ከዚህ ቀደም የሚገለገሉበት አውሮፕላን ልዑሉ እና ፖምፔዮ ወደ ሚነጋገሩበት ኔዮም ከተማ አቅንቷል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁም ወደ ሳዑዲ አድርገውታል ስለተባለው ጉዞ ምንም አይነት አስተያየት ከመስተት ተቆትበዋል።

አሜሪካ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማቃናት እየጣረች እንደሆነ እየተነገረ ሲሆን ሲሆን ይህ ውይይት የሚሳካ ከሆነ እንደ ታሪካዊ ጠላት በሚተያዩት አገራት መሪዎች መካከልም የመጀመሪያው የታወቀ ስብሰባ ይሆናል ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ እስራኤልን ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከባህሬን እና ከሱዳን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጀምሩና ስምምነት እንዲፈጠሩ ሠርተዋል።

ሳውዲ አረቢያ እርምጃዎቹን በጥንቃቄ ብትቀበልም በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል የሠላም ስምምነት እስኪደረግ ድረስ ከእስራኤል ጋር ከስምምነት እንደማትደርስ አስታውቃለች።

ይህ የእራኤልና የሳዑዲ መሪዎች በምስጢር ሊያደርጉት ነው የተባለውን ውይይት በተመለከተ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን በስፋት እየተነጋገሩበት ነው። ነገር ግን እሳካሁን የወጣ አስተማማኝ መረጃ የለም።

አስራኤል ለዘመናት በጠላትነት ከሚመለከቷት የመካከለኛው ምሥራቅ አጎራባቾቿና ሌሎች አረብ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል በአሜሪካ ድጋፍ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ያለውን ጥርጣሬና ስጋት ይቀርፈዋል ተብሎ ይታመናል።

እንደተባለው በአካባቢው ዋነኛዋ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆነችው ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ስምምነት መፍጠር ከቻለች ከሌሎቹ አረብ አገራት ጋር ለምታደርገው ቀጣይ መቀራረብ በር ከፋች ይሆናል ተብሎ ይታመናል።