ካቡል፡ በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ በተተኮሱ ሮኬቶች ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ

መኖሪያ አካባቢዎች ላይ በተተኮሱ ሮኬቶች በርካታ ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በርካታ ሮኬቶች በካቡል የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ተተኩሰው ቢያንስ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ ከ30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ የአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

በከተማው ውስጥ ከፒካፕ መኪና ላይ ከአስር በላይ ሮኬቶች እንደተተኮሱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። በዚህም በርካታ ሕንፃዎች እና ተሽከርካሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ታሊባኖች ከጥቃቱ ጀርባ አሉ መባላቸውን አስተባብለዋል።

ጥቃቱ የደረሰው የተጀመረውን የሰላም ድርድር ለመቀጠል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ እና የታሊባን ተደራዳሪዎች ከመገናኘታቸው ከሰዓታት በፊት ነው።

ተሰናባቹ የትራምፕ አስተዳደር በጥር ወር አጋማሽ 2000 ወታደሮችን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ማቀዱን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አስታውቆ ነበር።

ወታደራዊ ኃይሉን በከፍተኛ ፍጥነት መቀነስ የአፍጋኒስታን መንግሥት እንደገና የሚያንሰራራውን የታሊባንን እና ሌሎች ታጣቂዎችን የመቋቋም አቅሙን ያዳክመዋል በሚል ስጋት ተተችቷል።

እንደበርካታ ተንታኞች ከሆነ የውጭ ወታደሮች ከወጡ በኋላ ግጭቱ ከቀጠለ የአፍጋኒስታን ጦር በራሱ ለመመከት በቂ ጥንካሬ እንደሌለው ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ሮኬቶቹ ማዕከላዊ እና ሰሜናዊ ካቡልን መምታታቸው ተጠቁሟል። አካባቢዎቹ ብዛት ያላቸው ኤምባሲዎችን እና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የያሉበት ነው ተብሏል።

በካቡል የሚገኘው የኢራን ኤምባሲ ግቢው በሮኬት ፍንጣሪ የተመታ ቢሆንም በሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም ብሏል።

በማኅበራዊ ድር አምባዎች የተለቀቁ ቪዲዮዎች ላይ ሴት ተማሪዎች በፍርሃት እየጮኹ ከፍንዳታው አካባቢ ሲሮጡ አሳይተዋል።

አብዱልቃድር የተባሉ የዓይን እማኝ "ሮኬቶች ሲወርዱ ቁርስ እየበላሁ ነበር፤ አንደኛው ሮኬት የዳቦ መጋገሪያ ንብረት የሆነውን ተሽከርካሪ መቷል" ብሏል።

ታሊባን ባወጣው መግለጫ "በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ በጭፍን አንተኩስም" በማለት ተሳትፏል መባሉን አስተባብሏል።

አንድ ክልላዊ እስላማዊ ቡድን በአገሪቱ ውስጥ የሚሠራ ሲሆን በቅርብ ሳምንታት በካቡል ውስጥ ከተፈጸሙ ጥቃቶችን ጀርባ እንዳለ ተገልጿል።

ይህም በቅርብ ሳምንታት ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎችን የተገደሉባቸውና እና በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሱ ሁለት ጥቃቶችን ይጨምራል።

አሜሪካ ወታደሮችን ከአፍጋኒስታን ማስወጣት የጀመረችው በዚህ ዓመት የካቲት ወር አሜሪካ እና ታሊባን የተፈራረሙት ስምምነት አካል በመሆኑ ነው።

ሆኖም ቡድኑ ከአፍጋኒስታን መንግሥት ጋር የተጀመረው ድርድር በመቆሙ ጥቃቱን ሲያጠናክር በአገሪቱ ውስጥ ሁከት እየጨመረ መጥቷል።

ፖምፔዮ በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ከታሊባን እና ከአፍጋኒስታን ተወካዮች ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል። አሜሪካ እና ታሊባን እስካሁን ድረስ እየተወያዩ ባሉት የመጀመሪያ ጉዳዮች ላይ ለመፈራረም ተቃርበዋል የሚሉ አስተያየቶች አሉ።