"የወር አበባ ማየት የጀመርኩት 'ወንድ' ልጅ ሆኜ ነበር"

የፎቶው ባለመብት, Iryna Kuzemko, Lia and Olga Opinko
ኢንተርሴክስ የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል በተለምዶ የሴት ወይም የወንድ በሚል ከሚገለጸው የመራቢያ አካል ወይም መገለጫ በተለየ መንገድ የተወለዱ ሰዎችን ይገልጻል።
ለምሳሌ የአንድ ሰው ተክለ ሰውነት የሴት ቢሆንም መራቢያ አካሉ የወንድ ሊሆን ይችላል።
በመላው ዓለም በርካታ ኢንተርሴክስ ሰዎች አሉ። ብዙዎቹ ልጅ ሳሉ በቀዶ ህክምና አንድ ጾታ እንዲኖራቸው ይደረጋል። ይህ የቀዶ ህክምና ሂደት በጣም አወዛጋቢ ነው።
ኢንተርሴክስ የሚለው ቃል ከ40 በላይ የተለያዩ የሴት እና የወንድ ቁመናዎችን ያካትታል። አንዳንዶቹ ከዘረ መል መዋቅር ጋር የተያያዙ ሲሆን፤ ከተክለ ሰውነት ጋር የሚተሳሰሩም ይገኙበታል።
ብዙ ኢንተርሴክስ ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው በቀላሉ መልስ አያገኙም።
ሐኪሞች እንደሚሉት፤ የቀዶ ህክምና ሂደት ከመካሄዱ በፊት የዘረ መል ምርመራ ተደርጎ የአንድ ልጅ ጾታ እንዲታወቅ ይደረጋል።
ይህ የሚካሄደው በሐኪሞች፣ በልጆች ቤተሰቦችና በዘረ መል ባለሙያዎች ምክክር ነው።
በሌላ በኩል የኢንተርሴክስ የመብት ተሟጋቾች፤ ልጆች አስቸኳይ ካልሆነ ቀዶ ህክምና ሊደረግላቸው አይገባም ሲሉ ይከራከራሉ።
ሰው ስለጾታ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ የሚደርሰው ወይም የምትደርሰው በእድሜ ከፍ ካሉ በኋላ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ።
ሴት ወይም ወንድ የመሆን ውሳኔ የቤተሰብ ወይም የህክምና ባለሙያዎች መሆን የለበትም ብለውም ይከራከራሉ።
ቢቢሲ የሦስት ኢንተርሴክስ ሴቶችን የሕይወት ተሞክሮ እንደሚከተለው አቅርቧል።

የ27 ዓመቷ የመብት ተሟጋች ኢርንያ ኩምዜኮ
ያደግኩት እንደ ሴት ነው። ለአቅመ ሔዋን ስደርስ እንደ ጓደኞቼ የወር አበባ አላየሁም። ጡት ያላጎጠጎጥኩትም እኔ ብቻ ነበርኩ።
አንድ ቀን ስለ ሴቶች ጉልምስና የሚያስረዳ ፊልም ክፍል ውስጥ እያየን ነበር። ፊልሙ የሚገልጸው የእድገት ደረጃ እኔ ላይ አለመታየቱ አስጨነቀኝ።
እናቴና አያቴ እንደ ሌሎች ሴቶች አለማደጌ አላሳሰባቸውም። "አይዞሽ። ምንም አትሆኚም" ይሉኛል።
14 ዓመት ሲሞላኝ የማሕጸን ሀኪም ጋር ውሰዱኝ አልኳቸው። የማሕጸን ትቦዬ እንዲነቃቃ አንዳንድ ጥቆማ ተሰጠኝ።
ለወራት ያህል በሳምንት አንዴ የታዘዝኩትን እንቅስቃሴ አደረግኩ። ምንም ለውጥ አላመጣም። የበለጠ እጨነቅ ጀመር።
15 ዓመት ሲሞላኝ አባቴ ሞስኮ ለህክምና ወሰደኝ። እንዴት በፍጥነት ያልፉኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። ለእኔ ምንም ሳይሉኝ አባቴን ጠሩት።
አባቴ መጠነኛ ቀዶ ህክምና ማድረግ አለብሽ አለኝ። ምን እያደረጉኝ እንደሆነ አላወቅኩም ነበር። ከዚያ አባቴን ሰውነቴ ውስጥ ያለውን ማስወገድ ይሻለኛል ስለው ሐኪሞቹ እንዳወጡት ነገረኝ።
ተማሪ ሳለሁ ቁጡና ራሴን የምጠላ ሰው ነበርኩ።

የፎቶው ባለመብት, Iryna Kuzemko
ስለ ኢንተርሴክስ ቪድዮ ስመለከት ከእኔ ታሪክ ጋር እንደሚመሳሰል አስተዋልኩ። ከዚያም በ22 ዓመቴ ሞስኮ ወደሚገኙት ሐኪሞች ደወልኩ።
ከሰባት ዓመት በፊት የዘር ፍሬ እና የማሕጸን ቱቦ ያለው ህዋስ ሐኪሞቹ እንዳስወገዱ አወቅኩ። ከቀዶ ህክምናው በኋላ ሆርሞን እወስድ ነበር።
የወንድ እና የሴት ክሮሞዞም እንዲሁም ማሕጸን እንዳለኝም ተረዳሁ።
አባቴ ሁለት የልጆች ሥነ ልቦና ባለሙያዎች ስለ ቀዶ ህክምናው እንዳይነግረኝ እንደመከሩት ነገረኝ።
አባቴ መሳሳቱን አላመነም። እውነቱን ቢነግረኝ ኖሮ ሕይወቴ ይለወጥ ነበር። ከዚያ በኋላ አዋርቼው አላውቅም።
ለጥቂት ቀናት በጣም ግራ ተጋብቼ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ራሴን ተቀበልኩት።
ሌሎች ኢንተርሴክስ ሰዎችም በሰላም ይኖራሉ። በራስ መተማመኔ ጨምሯል። ሌሎች ልጆች እኔ ያለፍኩበት እንዳይገጥማቸውም አማክራለሁ።

የልጆች ሐኪሟ ጁልያ ሲዶሮቫ ምን ይላሉ?
የአንድ ልጅ ሕይወት አደጋ ውስጥ ሲወድቅ የሚካሄድ ቀዶ ህክምና ተለይቶ መታወቅ አለበት። 'ኮስሚክ ሰርጀሪ' በመባል የሚታወቀው የልጆች የመራቢያ አካልን በአንዳች መልክ ሲለወጥ ነው።
ለምሳሌ አንዲት ሴት ልጅ የውጪ የመራቢያ ክፍሏ የወንድ ቅርጽ ሊኖረው ይችላል። ይህ የተለመደውን የሴት መራቢያ አካል እንዲመስል ያደረጋል።
ይሄ ለሕይወት ባያሰጋም የሥነ ልቦና ጫና ሊያስከትል ይችላል። ታዳጊዋን ሌሎች ልጆች ለይተው እንዲመለከቷት ያደርጋል።
ለመሽናት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው አጋጣሚዎች ግን ቀዶ ህክምና አስፈላጊ ነው።
ሁሉም ልጅ ስለ ሰውነቱና ጾታው የመምረጥ እድል ሊሰጠው ይገባል። ይህንን አድገው ማገናዘብ ሲችሉ መወሰን ይችላሉ።
ቀዶ ህክምናው የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትልበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ስሜት ማጣት፣ መውለድ አለመቻል እና ከባድ ህመም። የሆርሞን ህክምና ለካንሰር ያጋልጣል።
ኢንተርሴክስ ከሆኑ ሰዎች መካከል ተቃራኒ ጾታ የሚማርካቸው፣ ተመሳሳይ ጾታ የሚማርካቸውም አሉ።
ቤተሰብ መስርተው፣ ልጅ ወልደው የሚኖሩ አሉ። ከክሮሞዞም ጋር የተያያዘ ሲሆን መውለድ የማይችሉም አሉ።
እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ተሞክሮ አለው። አንዳንዶች ቅይጥ ጾታ እንዳላቸው የሚታወቀው ሲወለዱ ነው። አንዳንዶች ደግሞ የተለየ ተክለ ሰውነት አላቸው።
እኔ ኢንተርሴክስ መሆኔን መቀበል ከጀመርኩ ወዲህ ደስተኛ ሆኛለሁ። በቅርቤ ያሉ ሰዎችም ይደግፉኛል፤ ይወዱኛል።

የሊያ ታሪክ
ስወለድ መራቢያ አካሌ እንዳልጎለበተና የወንድም የሴትም እንደማይመስል ሐኪሞች ለእናቴ ነገሯት።
እናቴ ሴት ብላ አስመዘገበችኝ። ያ ሐኪሞች የሠሩት የመጀመሪያው ስህተት ነበር።
እናም እንደ ሴት አሳደጉኝ። አንድ ቀን እናቴ የልጆች ሐኪም ቤት ስትወስደኝ 'ልጅሽኮ ወንድ ነው' አሏት።
ሌሎች ሐኪሞችም ይህንን ስላረጋገጡ ስሜ ተቀየረ። አንደኛ ክፍልም ወንድ ተብዬ ተመዘገብኩ።
መዋለ ሕጻናት የሚያውቁኝ ልጆች ሴት እንደነበርኩ ስለሚያስታውሱ እናቴ ሌላ ትምህርት ቤት ነበር ያስገባችኝ።
ያኔ ብዙም ሁኔታዬ አያስጨንቀኝም ነበር። ሰዎች ስለእኔ ሲብሰለሰሉ ሳይ ግን እኔም ማሰብ ጀመርኩ።

የፎቶው ባለመብት, Lia
ረዥም ጸጉሬን አልቆረጥም አልኩ። ሱሪና ሰፊ ልብስ እለብስ ነበር። አሁንም አለባበሴን አልቀየርኩም።
አሁን ላይ ጾታዬን መምረጥ እንደሌለብኝ ስለነገሩኝ ቀለል ብሎኛል።
13 ዓመቴ ላይ ፈረስ ገጭቶኝ ሆስፒታል ገባሁ።
አከርካሪዬ ተሰንጥቆ ነበር። ካቲተር ሲያስገቡልኝ ሴት ወይም ወንድ ልሁን እንደማይታወቅ እያወሩ ነርሶቹ ተሳለቁብኝ።
ከሆስፒታል ወጥቼ እንድ ዓመት ቤት ተኝቻለሁ። እናቴ፣ አያቴ እና እህቴ ቀኑን ሙሉ ይሠሩ ነበር። አባቴ ትቶን ሄዷል።
ማንም የሚንከባከበኝ አልነበረም።
አንድ ቀን በጣም ከመታመሜ የተነሳ ራሴን በመቀስ ወጋሁ። ከዚያ በኋላ ራሴን መጉዳት ጀመርኩ። እናቴ ይህን አላስተዋለችም።
ሐኪሞቹ እንደምድን አልጠበቁም ነበር። እኔ ግን የአካል ማጎልበቻ እየሠራሁ ያለ ድጋፍ መንቀሳቀስ ጀመርኩ።
ድሮ ከቤት ትምህርት ቤት ለመሄድ 20 ደቂቃ ይወስድብኝ ነበር። ከአደጋው በኋላ ግን 2 ሰዓት ይፈጅ ጀመር።
ትምህርት ቤት ልጆች መከራዬን አሳዩኝ። ቦርሳዬን ሽንት ቤት ይጥሉት ነበር። ሮጪ እንደማልደርስባቸው ስለሚያውቁ ተደፋፈሩ።
ልክ 16 ዓመት ሲሆነኝ አንድ ቀን ጠዋት አልጋዬ ላይ ደም አየሁ።
ሐኪም ቤት ተወሰድኩ። ከአልትራሰውንድ በኋላ ሐኪሚ 'ማሕጸን አለ' ሲል ሰማሁ።
የሴት መራቢያ አካል እንዳለኝ ያወቅኩት ያኔ ነበር። ወንድ ሆኜ የወር አበባ ማየት ጀመርኩ።
ሰውነቴ ውስጥ ያለውን፣ የማላየውን አካል እንዲያወጡት ፈልጌ ነበር።
ሆኖም ግን ሐኪሞቹ ውስጣዊ የሰውነት ክፍሌ መውጣት እንደሌለበት እና አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ አሳመኑን።
ከዚያም በሁለት ዓመት አራት ቀዶ ህክምና አድርጌ ሴት ሆንኩ።

የልጆች ሐኪሟ ጁልያ ሲዶሮቫ ምን ይላሉ?
አንድ ሰው በ14 ዓመቱ ወይም ዓመቷ ኢንተርሴክስ መሆናቸው ሲነገራቸው ምን ሊሰማቸው እንደሚችል አስቡት? ያውም በተገቢው መንገድ ሳይገለጽላቸው ሲቀር ደግሞ ያሳዝናል።
እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር ቤተሰቦች ጫና ያድርባቸዋል። እናት እርጉዝ ሳለች ታጨስ ወይም ትጠጣ ነበር? ወይስ በቤተሰቡ መካከል ዝምድና ነበር? ተብሎ ይጠየቃል።
ነገር ግን ኢንተርሴክስ ልጆች የመወለድ እድላቸው ሰፊ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው፤ ከጠቅላላ ሕዝቡ መካከል 1.7 በመቶ በሚጠጉት ላይ 40ው የኢንተርሴክስ አይነት በአንዱ ይካተታሉ።
እኔ ሴት እና ወንድ ልጅ አለኝ።
ወንድ ልጄን የወለድኩት በ20 ዓመቴ ነው። እንደ ጓደኛሞች ነን። ሴት ልጄ መዋዕለ ሕጻነት ተማሪ ሳለች አባቷ ጠልፎ ሌላ ከተማ ወስዷታል።
በሕይወቴ ብዙ ሴቶች፣ ወንዶችም ተዋውቄያለሁ። የሚማርኩኝ ሴቶች ናቸው።
አራት ጊዜ አግብቻለሁ። ለአምስተኛ እየተዘጋጀሁ ነው። የማገባው ጾታ የቀየረ (ትራንስጀንደር) ወንድ ነው።
እናቴ ለእኔ ትክክለኛውን ስለመምረጧ ዛሬም ትጠይቃለች። ከዚህ በኋላ ጥፋተኛነት ሊሰማት አይገባም።

የ35 ዓመቷ የመብት ተሟጋች ኦልጋ ኦንፒኮ
ሴት ነው የምመስለው። መጀመሪያ ላይ ሰውነቴም የሴት አካላት ነበሩት።
ወጣት ሳለሁ ሰውነቴ ጨመረ። ያኔ ሰው ያንጓጥጠኝ ጀመር። ቀንም ሌሊትም ብሮጥም ሰውነቴ ሊቀንስ አልቻለም።
24 ዓመት ሲሞላኝ የሆርሞን ምርመራ አደረግኩ። የሰውነት ሥርዓቴ የተዛባ እንደሆነ ተነገረኝ። ኢንተርሴክስ ምን እንደሆነ ግን አላውቅም ነበር።
የተዛባውን ለማስተካከል ሆርሞን ታዘዘልኝ። ከዚያ ግን ከከንፈሬ በላይና አንገቴ ላይ ጸጉር ማብቀል ጀመርኩ።
ወጥታ ከጓደኖቿ ጋር መዝናናት የምትፈልግ የ25 ዓመት ሴት ምን ሊሰማት እንደሚችል አስቡት?
ሆርሞኑን መውሰድ አቆምኩ። ሐኪሞች ጋር መመላለስ ግን አልተውኩም።
ከአራት ዓመት በፊት አንድ ሐኪም ክሮሞዞሜን አጥንቶ የወንድ እንደሆነና ኢንተርሴክስ መሆኔን ገለጸልኝ።
ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ እንደሆንኩ ያወኩት በ24 ዓመቴ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Olga Opinko
ወጣት ሳለሁ ለምን አልቀጥንም? ብዬ እጨነቅ ነበር። ሴት ነኝ? ስልም አስብ ነበር።
ወንድሜ ኢንተርሴክስ መሆኔን ሲሰማ ደስ አለው። ቤተሰቦቼ ተቀብለውኛል፤ ይወዱኛል። ግን ስለ ጉዳዩ ማውራት አይችሉም።
የፍቅድ ጓደኛዬ እንደ ወንድም እንደ ሴትም ራሷን አታይም።
ማኅበረሱ ውስጥ ልዩነት በበጎ ሁኔታ አይታይም። ኢንተርሴክስ ሰዎች ሰሚ ማግኘት አለባቸው
በልጅነታቸው ቀዶ ህክምና ተደርጎ ሕይወታቸው የተመሳቀለባቸው አሉ።
ቤተሰቦችና ሐኪሞች ቅይጥ ጾታ ያላቸው ልጆች ወደ አንድ ጾታ እንዲያደሉና ወንድ ወይም ሴት እንዲሆኑ ይፈልጋሉ።
ኢንተርሴክስ የሆኑ ሰዎች መገለል፣ እንግልት ይደርስባቸዋል።
ተፈጥሮ እኛ በምናስበው ጾታ ብቻ እንደማይገለጽ መረዳት አለብን።

የሥነ ልቦና ባለሙያ ሼሪ ኪሪሊክ ምን ይላሉ?
ኢንተርሴክስ ታካሚዎች አሉኝ።
ልጅ ሳሉ የተካሄደውን ቀዶ ህክምና ሲያውቁ በጣም ይበሳጫሉ። ይህ ቁጣ ራሳቸውን እንዳያሳጣቸው መደረግ አለበት።
ራሳቸውን ተቀብለው ልዩ መሆናቸውን ሲገነዘቡ፤ ውበታቸው ይታያቸዋል። ፊታቸው ማብራት ይጀምራል።












