ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማማረር አብዝተው የሚወዱት የአውሮፓዊት አገር ዜጎች
ፈረንሳይውያን አብዝተው ቅሬታ ማቅረብን ያዘውትራሉ። እንደውም ፈረንሳይ ውስጥ ማማረር የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ ወሬ እንደማስጀመሪያም ጭምር ነው የሚታየው።
ነገር ግን መቼ ነው ሰዎች የሚያማርሩት፣ ለማን ነው የሚያማርሩት እና ስለምንድነው የሚያማርሩት የሚለው በራሱ ጥበብ ነው።
አብዛኛው የፈረንሳያውያን ንግግር የሚጀምረው በረጅሙ በመተንፈስና በመከፋት ስሜት ነው። "ዛሬ የአየር ጸባዩ መጥፎ ነው"፣ "ፖለቲከኞቻችን ራስ ወዳድ ናቸው" የሚሉ አስተያየቶችን መስማት የተለመደ ነው።
በፈረንሳይኛ ቋንቋ ቅሬታን ለማቅረብ የሚረዱ ወይም ቅሬታን የሚገልጹ በርካታ ቃላት አሉ። በተደጋጋሚ ለማማረር የሚረዱ፣ ይፋዊ ቅሬታ ለማቅረብ የሚረዱና እንደው ለነገሩ ምሬት ለመግለጽ የሚረዱ ቃላት በሽ ናቸው።
ፈረንሳይ ውስጥ በሚገኘው አውስትራሊያን ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር የሆኑት ዶክተር ጌማ ኪንግ እንደሚሉት ሰዎች በተደጋጋሚ አንድን ነገር ማድረግ እንደማይፈልጉ ሲናገሩ ሊደመጡ ይችላሉ፤ ነገር ግን ያንን ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም።
ለፈረንሳያውያን ማማረር ተገቢ ነገር ነው፤ በተዳጋጋሚም ይደረጋል፤ ንግግር ማስጀመሪያም ነው። የሆኑ ጓደኛማቾች ሰብሰብ ብለው በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ ስላሉት ምርጥ ምርጥ ምግቦች ማውራት ቢጀምሩ ወዲያውኑ ርዕሱ ወደ ማማረር ሊቀየር ይችላል።
ድንገትም ምግብ ቤቱ በጥሩ ሁኔታ ስለማያዘጋጃቸው ምግቦችና አጠቃላይ ችግሮቹ ሁሉም ሰው ሊያወራ ይችላል።
አንድ ሰው አዲስ ቤት ተከራይቶ ወይም ገዝቶ ለጓደኞቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በደስታ ተውጦ ቢነግራቸው ምንልባትም አብዛኛዎቹ ሰዎች ቤቱን ለማሰናዳት መጋረጃ ስለመግዛት፣ ወንበርና ጠረጴዛ ስለማመቻቸትና የመሳሰሉ ነገሮችን አንስተው ሊያማርሩ ይችላሉ።
ፈረንሳይ ውስጥ ሰዎች ስለሁሉም ነገር ያማርራሉ ማለት ግን አይደለም። ምናልባት የንግግሩ መጀመሪያ አልያም መጨረሻ ማማረር ሊሆን ይችላል ነገር ግን ይህ በራሱ ማስተዋልን የሚጠይቅ ነገር ነው።
ሰዎች ስለአንድ ነገር ነቀፌታቸውን አልያም መጥፎ ባህሪ ነው ብለው የሚያስቡትን ነገር ሲናገሩ ምን ያክል ነገሮችን እንደሚያስተውሉና በተለየ መንገድ እንደሚመለከቱ ማስረጃ ሊሆንም ይችላል።
ፈረንሳያውያን የሚያማርሩበት መጠን ለሌሎች አውሮፓውያን ምቾትን የሚነሳ ነገር አንደሆነም ይነገራል። አብዛኛዎቹ እንደሚሉት ስለመጥፎ ነገር ባወራን ቁጥር መጥፎ ነገር ይከተለናል።
ነገር ግን አንዳንድ ባለሙያዎች ፈረንሳያውያን ሕይወታቸውን የሚመሩበት መንገድ ለጤና ጥሩ ነው ብለው ያምናሉ።
በአውሮፓውያኑ 2013 የተሰራ አንድ የስነ አእምሮ ጥናት መሰረት ሰዎች ስለነገሮች ያሏቸውን መጥፎ አመለካከቶች አልያም ተሞክሮዎች በገለጹ ቁጥር ከአንዳንድ የውስጥ ደዌ በሽታ እራሳቸውን ይከላከላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ 2011 ላይ በአሜሪካው ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት ሰዎች የሚሰሟቸውን መጥፎ ስሜቶችና ቅሬታዎች ወደውስጣቸው የሚያስቀሩ ከሆነ ቁጡና ተናዳጅ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።
ይህ ማለት ግን ሁልጊዜ ማማረር ጥሩ ነው ማለት አይደለም። ሁሌም ባማረርን ቁጥር ጭንቅላታችን የነገሮችን ጥሩ ጎን ከመያት ይልቅ በሁሉም ነገር ላይ መጥፎውን ብቻ ነቅሶ እንዲየወጣና ደስተኞች እንዳንሆን ሊያደርገን ይችላል።
ነገር ግን ፈረንሳዮች ከዚህ አይነት አሰልቺ ነገር የራቁ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛዎቻቸው የሚያማርሩት ስለራሳቸው ሕይወት አይደለም። ብዙውን ጊዜ ሲያማርሩ የምታገኟቸው ስለውጪያዊ ነገር ነው።
በፈረንሳይ በአንድ ወቅት በተሰበሰበ ድምጽ መሰረት 48 በመቶ የሚሆኑት ፈረንሳያውያን ብዙ ጊዜ የሚያማርሩት ስለመንግስት ነው። ለምሳሌ እንኳን በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ፈረንሳያውያን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየወሰዷቸው ባሏቸው እርምጃዎች ደስተኞች አይደሉም።
በዚህም ምክንያት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ፈረንሳያውያን በፕሬዝዳንቱና በፖሊሲዎቻቸው ዙሪያ ሲያማርሩና ነቀፌታቸውን ሲገልጹ ነው የሚውሉት።
በአጠቃላይ ፈረንሳያውያን ስለራሳቸው የግል ሕይወት ሲያማርሩ እምብዛም አይታዩም። በዚሁ በተሰበሰበው ድምጽ መሰረት 23 በመቶ የሚሆኑት ፈረንሳያውያን ወዳጅ ዘመዶቻቸው ለምን ስልክ እንደማይደውሉላቸው በመጠየቅ እንደሚያማርሩ ገልጸዋል።
33 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ስልካቸውን አልያም ቁልፋቸውን ማግኘት ስላለመቻላቸው የሚያማርሩ ሲሆን ቀሪዎቹ 12 በመቶዎች ደግሞ ስልጆቻቸው ምርር ብለው እንደሚያወሩ ገልጸዋል።
በቤልጂየሙ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ማርጎት ባስቲን በበኩላቸው ፈረንሳያውያን የሚያማርሩት የሆነን ነገር ለመቀየር አልያም ለውጥ ለማምጣት አይደለም ይላሉ።
''እነሱ ትኩረታቸውን የሚያደርጉት ውስጣቸው ያለውን አሉታዊ ስሜት ማውጣትና ማራገፍ ላይ ነው። የሆነን ነገር ለመቀየር ብለው አይደለም የሚያማርሩት፤ ስለጉዳዩ ማውራት ስላለባቸው ብቻ ነው የሚያማርሩት'' ይላሉ።