የኮቪድ-19 ክትባትን እየሠራ ያለው ኩባንያ የበይነ መረብ ጥቃት ደረሰበት

ታትሟል

የኮቪድ-19 ክትባትን እየሠራ የሚገኘው ዶ/ር ሬዲሰ የተባለው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ በኮምፒውተር መረጃ መዝባሪዎች ጥቃት እንደደረሰበት ገልጿል።

ኩባንያው በምርምር ቦታዎቹ በተለይም እንግሊዝን ጨምሮ በብራዚል፣ ሕንድ፣ ሩሲያ እና በአሜሪካ ያሉት ጥቃት ደርሶባቸዋል።

የኩባንያው የሕንድ ቅርንጫፉ ከበይነ መረብ ጥቃቱ ለማምለጥ ራሱን አግልሎ በራሱ መረጃ ቋት እየተጠቀመ መሆኑን ገልጿል።

ዶ/ር ሬዲስ፤ ስፖትኒክ ቪ ኮቪድ-19 የተሰኘውን የሩሲያ ክትባቱን የመጨረሻ ሙከራውን እንዲያከናውን ባለፈው ሳምንት ፈቃድ አግኝቷል።

መረጃዎቹ ላይ ጥቃት ስለመድረሱ ግን ኩባንያው መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

በእንግሊዝ የኩባንያው የስልክ መስመሮች በተለይም ካምብሪጅሻየር እና ዮርክሻየር የሚገኙት ተቋርጠዋል። ነገር ግን ይህ ከጥቃቱ ጋር ስለመገናኘቱ ኩባንያው ያለው ነገር የለም።

በኩባንያው ዓለም ዓቀፍ ዋና የመረጃ ኃላፊ የሆኑት ሙከሽ ራቲ፤ "የሳይበር ጥቃት እየደረሰብን መሆኑን እንዳወቅን ሁሉንም መረጃዎቻችንን ለይተናል። ክስተቱን ተከትሎ በ24 ሰዓታት ውስጥ ሁሉንም አገልግሎቶቻችን ላይ ቅኝት አድርገናል። እናም ያን ያክል የጎላ ጥቃት አልደረሰብንም" ብለዋል።

በሕንድ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች በተወሰኑ የዶ/ር ሬዲስ ምርቶች መስተጓጎላቸውን ዘግበዋል።

ዶ/ር ሬዲስ በ1986 የተቋቋመ ሲሆን፤ መቀመጫውን ሃይደራባድ አድርጓል። በአሁኑ ወቅትም ከ200 በላይ መድኃኒቶችን ያመርታል።

በእንግሊዝ መቀመጫውን ቤቨርሌይ ዮክሻየር አድርጎ ለአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር የመድኃኒት አቅራቢ ነው።

ባለፈው ሳምንት ኩባንያው እና የሩሲያ የውጭ ሀብት ፈንድ፤ በሕንድ ስፑትኒክ ቪ ኮቪድ-19 ክትባትን በሕንድ ውስጥ የሰው ክሊኒካል ሙካራ ለማድረግ ከሕንድ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጸው ነበር።