ኢትዮጵያ- በርካቶች ጋር መድረስ የቻለው የትዊተር ዘመቻ

ታትሟል

ከትናንት በስቲያ ኢትዮጵያን የተመለከተ እና ለ24 ሰዓታት የዘለቀ የትዊተር ዘመቻ ተካሂዷል።

በዚህ ዘመቻ ጥቅም ላይ የዋሉት ሃሽታጎች (የዘመቻ ሐረጎች) ከ40 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ጋር መድረሳቸውን የትዊተር አናሊቲክስ ድረ-ገጾች ያመላክታሉ።

ከትናንት በስትያ (ሐሙስ) በተካሄደው የትዊተር ዘመቻ ላይ ሁለት ዋነኛ ሃሽታጎች ጥቅም ላይ ውለው ነበር። #300Lives3Months (300 መቶ ህይወቶች በ3 ወር ውስጥ) እና #ProblmeIsTyrannyNotEthnicity (ችግሩ የብሄር ሳይሆን አምባገነንነት ነው) የሚል ይዘት ያላቸው መሪ መፈክሮች ተጋርተዋል።

ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመዳሰስ የሚታወቀው ቶክዎከር (Talkwalker) ድረ-ገጽ ላይ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ጥቅምት 12 እና 13 ላይ #300Lives3Months የተሰኘው ሃሽታግ 44.5 ሚሊዮን ትዊተር ተጠቃሚ ሰዎች ጋር ደርሷል።

239 ሺህ ሰዎች ደግሞ #300Lives3Months የሚለውን ሃሽታግ የያዘን ትዊት ክሊክ አድርገዋል፣ አጋርተዋል፣ መውደዳቸውን አሳይተዋል (ላይክ አድርገዋል)፣ ተከትለዋል፤ አልያም አስተያየት ሰጥተውበታል።

ከዘመቻው አስተባባሪዎቹ አንዱ የሆነው ኣየስፔድ ተስፋዬ ከሁለቱ ሃሽታጎች በተጨማሪ ተመሳሳይ መልዕክት የሚያስተላልፉ 'ሶማሌ'፣ 'ምስራቅ ሃረርጌ' እና 'ምዕራብ ሃረርጌ' የሚሉ ሃሽታጎች ጨምሮ ከትዊተር አናሊቲክስ መረዳት እንደቻልነው 1.1 ሚሊየን ጊዜ ትዊት እና ሪትዊት ተደርጓል ይላል።

ዓለማው ምንድነው?

የዘመቻው አስተባባሪ ከሆኑት መካከል ሌላኛው ሳሙኤል በቀለ፣ የትዊተር ዘመቻው ዋነኛ ግብ "በኢትዮጵያ እየሆነ ስላለው ሁኔታ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ነው" ይላል።

ሳሙኤል "መንግሥት ከውጪ የሚገኘውን ድጋፍ ከተፈቀደለት ዓላማ ውጪ እየተጠቀመ ነው። ይህንንም የውጪው ማህብረሰብ እንዲያውቅ ዘመቻውን አስፈልገወል" ይላል።

#300Lives3Months

የትዊተር ዘመቻው አስተባባሪዎች ባለፉት ሦስት ወራት 300 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል ይላሉ። እያስፔድ ተስፋዬ በትዊተር ዘመቻ ላይ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ ሟቾችን ማንነት በሥም፣ የተገደሉበትን ስፍራ እና በቀን ለይተን አስቀምጠናል ይላል።

"በነገራችን ላይ ባለፉት 3 ወራት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ300 በላይ ነው። 'ሴንሰቲቭ' ያልናቸውን መርጠን ነው እንጂ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚያ በላይ ነው" ሲል አክሏል።

ከ300ዎቹ ሰዎች ከፍተኛ ድርሻውን የሚይዙት በመንግሥት የጸጥታ ኃይል የተገደሉ ናቸው የሚለው እያስፔድ፤ "ከተገደሉት መካከል የ8 እና የ9 ዓመት ልጆች እንዲሁም በመኖሪያ ቤታቸው ተኝተው ሳለ የተገደሉ የሃይማኖት አባቶች አሉ" ሲል ለቢቢሲ አስረድቷል።

#ProblmeIsTyrannyNotEthnicity

እያስፔድ በኢትዮጵያ ዋነኛው ችግር አምባገነንነት ነው እንጂ የብሔር ጉዳይ አይደለም ይላል።

"መንግሥት እየወሰዳቸው ላሉት ያልተመጣጠኑ የኃይል እርምጃዎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች 'የብሔር ግጭት' የሚል ምክንያትን እንደ መሸፈኛ እየተጠቀመበት ይገኛል" ሲልም ያብራራል።

ሕይወታቸውን ካጡት እና በዘመቻው ከተጠቀሱት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ምንም አይነት የብሔር ግጭት ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ መሆናቸውንም ይገልጻል።

ለዚህም እንደ ምሳሌ የወላይታን ጉዳይ በማንሳት፣ መንግሥት "ሕገ-መንግሥታዊ የሆነውን የክልልነት ጥያቄ በመመለስ ስልጣንን ያልተማከለ ማድረግ ስላልፈለገ ብቻ በርካቶች ተገድለዋል። ይህንን በዘመቻችን ውስጥ አካትተነዋል" ብሏል።

ሰኔ 3 2012 ዓ.ም. ከወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በጸጥታ ኃይሎች በተያዙ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሰበብ በተከሰተ አለመረጋጋት ቢያንስ የ16 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።

ዞኑን በክልልነት ለማደራጀት ከተቋቋመው ሴክሬታሪያት ጋር ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የህግ ባለሙያዎችና የአገር ሽማግሌዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ነበር ችግሩ የተከሰተው።

በወቅቱ የደቡብ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች "የክልል እንሁን ጥያቄ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንዳይፈታ ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው" ሲሉ ለአገር ውስጥ መገናኛ ተናግረዋል።

"ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መንስዔው የፖለቲካ ቀውስ ነው"

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚነሱት ሁሉ በሚገለጸው ልክ ትክክል ናቸው ማለት ባይቻልም፣ በኢትዮጵያ አሳሳቢ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳዮች መኖራቸውን ይናገራሉ።

"በእኛ በኩል ማለት የምችለው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ፤ ሰፊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ችግር አለ" ለቢቢሲ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሩ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሪፎርም ሥራ እያከናወን መሆኑን አስታውሰው፣ ባለው አቅም የሚደርሱትን ጥቆማዎች መርምሮ መፍትሄ እና ምክረ ሃሳብ እየሰጠ መሆኑንም ገልፀዋል።

ኮሚሽነር ዳንኤል "አብዛኛው የሰብዓዊ መብት ችግር የሚመነጨው ከፖለቲካ ቀውሳችን ነው" ካሉ በኋላ፣ የፖለቲካ ቀውሱ በሚፈጥረው ግጭት የበርካቶች ሕይወት መጥፋቱን፤ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸውን እና ያለ አግባብ መታሰራቸውን ይናገራሉ።

"የጸጥታ ኃይሎችም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚሰሩ እናውቃለን። ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ፍልሚያ ያደርጋሉ። በዚህ መካከል የጸጥታ ኃይሎች እንደሚገደሉ እናውቃለን። ይህ የውስብስብ ፖለቲካችን መገለጫ ነው" ብለዋል።

ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግር መፍትሄ የሚያገኘው "የፖለቲካ ቀውሱ መፍትሄ ሲያገኝ ነው" የሚሉት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነሩ፤ "በመንግሥት በኩል ለፖለቲካ ችግሩ የፖለቲካ መፍትሄ እንዲፈለግለት እናሳስባለን፤ ምክረ ሃሳብ እንሰጣለን" ብለዋል።

የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ወስደዋል

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥስቶች እየተበራከቱ መጥተዋል ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የአምነስቲ የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ተክሌ በኦሮሚያ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሰላም ለማስፈን የተሰማሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ወስደዋል ይላሉ።

በዚህም የበርካቶች ሕይወት ማለፉን ይናገራሉ። እንደ ምሳሌም በኦሮሚያ ክልል፣ ባሌ ዞን ሮቤ ከተማ የተገደለውን ወጣት ያነሳሉ።

እሑድ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ. ም. ሮቤ ከተማ አንድ ወጣት ከፖሊስ በተተኮስ ጠይት መገደሉ ይታወሳል። የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ወጣቱ መገደሉን አረጋግጠዋል፤ ክስተቱ ሰልፍ ሳይሆን በከተማው ረብሻ ለመፍጠር የተደረገ ሙከራ ነው ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሰልፉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከ15-20 የሚጠጉ ወጣቶች "ጀዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ ይፈቱ የሚል" መፈክር እያሰሙ ሳለ ፖሊስ ተኩስ ከፍቶ እንደበተናቸው እና በዚያ መካከል ወጣቱ መገደሉን ተናግረዋል።

አምነስቲ ባለፉት ጥቂት ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተገደሉት ሰዎች ያለው መረጃ ምን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ፍሰሃ፤ በሐረርጌ ተካሂዶ በነበረው ተቃውሞ ቢያንስ 20 ሰዎች ተገድለዋል፤ በወላይታ ዞን ደግሞ ቢያንስ 16 ሰዎች በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይል ተገድለዋል በማለት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በጉጂ፣ ቦረና እና ምዕራብ ወለጋ በተመሳሳይ ግድያዎች እየተፈጸሙ እንደነበረ መረጃው አለን ሲሉም አቶ ፍሰሃ ያብራራሉ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ደግሞ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት በርካቶች ስለመገደላቸው መረጃው እንዳላቸው እና ተጨማሪ ጥናቶችን እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ቢያንስ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች በታጣቂዎች በማለትም፣ በደቡብ ክልል ደግሞ በቤንች ማጂ ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።

በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ እንደተባለው 300 ሰዎች ስለመገደላቸው ግን የተጣራ መረጃ እንደሌላቸው እና አሁንም ምርመራ እያደረጉ መሆናቸው ይናገራሉ።

አቶ ፍሰሃ መንግሥት የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ቁርጠኝነት ካለው ከተመጣጣኝ በላይ የሆነ እርምጃ የወሰዱ ኃይሎችን ለሕግ ማቅረብ ይኖርበታል ሲሉም ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።

የአንድም ሰው ሕይወት ማለፍ የለበትም

የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍ እና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ጉዳዩን በሚመለከት ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ባለፉት ዓመታት ሁለት ችግር ማጋጠሙን ተናግረዋል።

በእነዚህ ችግሮች ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ የወጡ፣ " ችግር ለመፍጠር" የተንቀሳቀሱ፣ እንዲሁም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

መንግሥት የአንድም ሰው ሕይወት ማለፍ የለበትም ብሎ አንደሚያምን የተናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ቢቀለ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ "አላስፈላጊ እርምጃ በመውሰድ የሰው ሕይወት እንዲያልፍ ያደረገ በሕግ መጠየቅ አለበት" ብለዋል።

እንደ ዶ/ር ቢቀለ ከሆነ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ በመውሰድ የሰው ሕይወት እንዲያልፍ ያደረጉ አካላት እየተጠየቁ ሲሆን "መንግሥት እያጣራ የሕግ እርምጃ መውደሱን ይቀጥላል" ሲሉም ተናግረዋል።

ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አክለውም በየትኛውም ቦታ በግጭቶች መካከል የሰው ሕይወት ሲያልፍ የሚኖርበት ዞን፣ወረዳ እንዲሁም ቀበሌ እና ሕይወቱ ያለፈበት ምክንያት ከአስከሬን ምርመራው ከተረጋገጠ በኋላ ይመዘገባል።

"በዚህ ውስጥ ኃይል እርምጃ የወሰደ አካል ይጠየቃል። ሌሎች አካላትም ወንጀል ሊፈጽሙ ይችላሉ። ይህም መጣራት አለበት ብዬ አምናለሁ" ሲሉም አክለዋል።

በመጨረሻም በተለያዩ ጉዳዮች 'መጓተቶች ቢኖሩም' የማጣራት ስራው ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ ብለዋል ዶ/ር ቢቂላ።