ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርሜንያ እና አዘርባጃን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ እየተወነጃጀሉ ነው
አርሜንያ እና አዘርባጃን በንጹሀን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት የተስማሙትን የተኩስ አቁም ስምምነት አንደኛዋ አንደኛዋን ጥሰሻል በማለት ከአሁኑ መወነጃጀል ጀምረዋል።
ናጎርኖ- ካራባክ ተብሎ በሚታወቀው አወዛጋቢ ክልል ውስጥ የአርሜንያናና የአዘርባጃን ወታደሮች መጋጨታቸው የሚታወስ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ካለፈው ከቅዳሜ ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው ነበር።
የአርሜንያ መከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባዩዋ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ በተደረገ ደቂቃዎች ውስጥ አዘርባጃን ሮኬቶችን እና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም ጥቃት ፈጽማለች ብለዋል።
አዘርባጃን በበኩሏ አርሜንያ ስምምቱን እንዳፈረሰች አስታውቃለች።
ሁለቱም አገራት በሩሲያ አሸማጋይነት ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት ነበር የተኩስ አቁም ስምምቱን ያደረጉት። ነገር ግን አሁንም ድረስ ግጭቶች እንደቀጠሉ ናቸው።
ናጎርኖ- ካራባክ የተባለውን ክልል ተከትሎ ለረዥም ዓመታት የቆየው ይህ የሁለቱ አገራት ፍጥጫ ባለፉት ወራት እንደገና ማገርሸት ጀምሯል።
ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይም በድንበር አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት 16 ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ነው።
አርሜንያ እና አዘርባጃን በጎሮጎሳውያኑ 1991 የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ከመፍረሷ በፊት ሁለቱም የሕብረቱ አካል ነበሩ።
ላለፉት አራት አስርት ዓመታትም ሁለቱም ይገባኛል በሚሉት ናጎርኖ- ካራባክ አካባቢ ሲጨቃጨቁ ቆይተዋል።
አካባቢው በአሁኑ ሰአት በአርሜንያ ብሄሮች ቁጥጥር ስር ይሁን እንጂ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ግን ቦታው የአርባጃን እንደሆን ተስማምቷል።
በጎሮጎሳውያኑ 2016 ተመሳሳይ ግጭት ተከስቶ ለአራት ቀናት የቆየ ጦርነት መሰል ውጊያ አካሂደዋል።
ሩሲያ ከአርሜንያ ጋር የጦር ሕብረት ያላት ሲሆን በአገሪቷም የጦር ሰፈር አላት። ይሁን እንጅ ከአዘርባጃን መንግሥት ጋርም የቅርብ ግንኙነት እንዳላት ይነገራል።
አርሜንያ ራስገዝ የሆነችውን ናጎርኖ- ካራባክህን የምትደግፍ ቢሆንም ይፋዊ እውቅና ግን አላገኘችም።
ግጭቱ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት -ኔቶ አባል አገራት በሆኑት ፈረንሳይና ቱርክ መካከልም ውጥረትን ፈጥሯል። ፈረንሳይ ለበርካታ አርሜንያዊያን መኖሪያ ስትሆን ቱርክ ደግሞ በአዘርባጃን የሚገኙ ቱርካዊያንን ትደግፋለች።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰተር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ፈረንሳይ "አርሜንያዊያንን ትደግፋለች" ሲሉ መክሰሳቸው የሚታወስ ሲሆን የፈረንሳዩ ፕሬዚዳነት ኢማኑኤል ማክሮንም ለዚህ የአፀፋ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ከቱርክ የሚመጡ 'ጦርነት ቀስቃሽ' መልዕክቶችን ተችተዋል።
ትናንት ቅዳሜ ጠዋት ላይ ሁለቱም አገራት አንደኛዋ አገር በሩሲያ አደራዳሪነት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምቱን ጥሳለች በማለት እርስ በርስ ተወነጃጅለዋል።
የአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው ስምምነቱ የተደረሰው አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ እንደሆነ አስታውቋል።