ኮሮናቫይረስ፡ ፈረንሳይ ሁለተኛ ዙር ወረርሽኙን ለመከላከል ሰአት እላፊ ልታውጅ ነው

ታትሟል

እንደ አዲስ ያገረሸውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ፓሪስን ጨምሮ በዘጠኝ ከተሞች የምሽት እንቅስቃሴን የሚገድብ የሰአት እላፊ አዋጅ ሊታወጅ መሆኑን የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስታውቀዋል።

ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የእንቅስቃሴ ገደብ ቢያንስ ለአራት ሳምንታት እንደሚቆይ የተገለጸ ሲሆን አስቸኳይ ብሄራዊ የጤና ስርአትም ተግባራዊ ይደረጋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጎረቤት አገር ጀርመን ለቫይረሱ ስርጭት ተጋላጭ ናቸው ያለቻቸውን እንደ ምግብ ቤትና መጠጥ ቤት ያሉ አገልግሎት መስጫዎች በጊዜ እንዲዘጉ ውሳኔ አስተላልፋለች።

አገሪቱ ካሳለፍነው ሚያዝያ ወር ወዲህ ከ5 ሺ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችነ ማግኘቷን ተከትሎ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርክል ትናንት ረቡዕ ዕለት ጠበቅ ያሉ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አስታውቀዋል።

በእያንዳንዱ 100 ሺ ነዋሪ 50 ሰው በቫይረሱ የተያዙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ምግብና መጠጥ ቤቶች ከምሽቱ አምስት ሰአት በኋላ እንዳይሰሩ የተነገራቸው ሲሆን ሰዎች በግል የሚያካሂዷቸው ዝግጅቶችም ቢሆን ከአስር ሰው በላይ እንዳይገኝባቸው ተብሏል።

በመላው አውሮፓ ደግሞ የአገራት መንግሥታት ሁለተኛ ዙር እንደ አዲስ እየተቀሰቀሰ ያለውን የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ለመዋጋት ይበጁኛል ያሏቸውን እርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛሉ።

ኔዘርላንድስ በግማሽ የእንቅስቃሴ ገደብ የታወጀ ሲሆን ምግብና መጠጥ ቤቶችም እየተዘጉ ነው።

በሰሜን ምስራቅ ስፔን የምትገኘው የካታሎን ግዛት ደግሞ ምግብና መጠጥ ቤቶች ከዛሬ ሐሙስ ጀምሮ ለሚቀትሉት 15 ቀናት ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ ተገልጿል።

ቼክ ሪፐብሊክ ደግሞ ትምህርት ቤቶችና መጠጥ ቤቶችን የዘጋች ሲሆን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአውሮፓ ከፍተኛ የተባለውን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ስታስመዘግብም ነበር።

እስካሁን ባለው አካሄድም በእያንዳንዱ 100 ሺ ነዋሪ 581.1 ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙባት ነው።

የአየርላንድ መንግስት ከዛሬ ጀምሮ ሰዎች ወደሌሎች ሰዎች ቤት ሄደው መጠያየቅ እንደማይችሉ አስታውቋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ያስታወቁት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዋና ከተማዋ ፓሪስ፣ማርሴ፣ ሊዮን፣ ሊል፣ ሴይንት ኢቴይን፣ ሮውን፣ ቶሉስ፣ ግሪኖብል አንዲሁም ሞንፕሌይር ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚተገበርባቸው ከተሞች የሚኖሩ እስከ 22 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ሕጉን ማክበር ያለባቸው ሲሆን የኢማኑኤል ማክሮን መንግስት በመጀመሪያ ያሰበው ለአራት ሳምንታት ነው። ነገር ግን እስከ ስድስት ሳምንታት ድረስ ለማራዘም እቅድ አለ ተብሏል።

በዚህም መሰረት ሰዎች በምሽት ምግብና መጠጥ ቤቶችን መጎብኝት የማይችሉ ሲሆን ወደ ሶወች ቤት መሄድም ቢሆን አይፈቀድም።