ኮቪድ-19፡የትራምፕ ታዳጊ ልጅ በኮሮናቫይረስ ተይዞ እንደነበር ተገለፀ

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የ14 ዓመት ልጅ፣ ባሮን በኮሮናቫይረስ ተይዞ እንደነበር እናቱ፣ ቀዳማዊት እመቤት ሜላንያ ትራምፕ ገልፃለች።

በአሁኑ ወቅት ግን ተመርምሮ ነጻ መሆኑንም አስረድታለች።

ሚላንያ ልጇ ባሮን ተመርምሮ በኮሮናቫይረስ መያዙን ስታውቅ "የፈራሁት ደረሰ" ማለቷን ትናገራለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕና ባለቤታቸው ሜላንያ እንዲሁም ሌሎች የዋይት ሐውስ ሰራተኞች በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት አገግመዋል።

ልጇ በቫይረሱ ተይዞ የነበረበት ወቅት እነሱም ታመው ከነበረበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ መሆኑንም ሜላንያ ትራምፕ በዋይት ሃውስ ድረ-ገፅ አስፍራለች።

ሜላንያ ስለ ልጇ በቫይረሱ መያዝ ይፋ ማውጣቷን ተከትሎም የምረጡኝ ቅስሳ ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ለአጭር ጊዜ ቫይረሱ ይዞት ነበር" ሲሉ የልጃቸውን የጤና ሁኔታ በአዮዋ ለተሰበሰበው ደጋፊያቸው ተናግረዋል።

"መያዙን ሁሉ የሚያውቅ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ገና ታዳጊ ስለሆነ እና የመከላከል አቅሙ ጠንካራ በመሆኑ በቀላሉ መክቶታል" ብለዋል።

አክለውም " ባሮን መልከ መልከ መልካምና ነጻ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የልጃቸውንም ከኮሮናቫይረስ በቀላሉ ማገገምም እንደ ምክንያት በመጥቀስ አሜሪካ ትምህርት ቤቶቿችን በቅርቡ ልትከፍት ይገባል ሲሉም ሞግተዋል።

በርካታ የመምህራን ማህበራት ግን በአሁኑ ሰዓት ትምህርት ቤቶች መከፈት እንደሌባቸውና በርካታ መምህራን በተማሪዎች ሊጠቁ ይችላሉም እያሉ ነው።

በአዮዋ ለተሰበሰው ደጋፊዎቻቸውም "ባሮን በኮሮናቫይረስ መያዙ ተነገረን። ከሁለት ሰኮንዶች በኋላ ተሻለው። አሁን ነፃ ነው አልተባለም? ተብሏል። ሰዎች በኮሮናቫይረስ ይያዛሉ፣ ይሻላቸዋል። ልጆችን ትምህርት ቤት መልሱ" ብለዋል።

በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የአለም መነጋገሪያ ሆነው የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ተመልሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተነገረ ሁለት ሳምንታት ባልሞላ ጊዜም ውስጥ ነው በሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በፍሎሪዳ፣ ሳንፎርድ ከአዳራሽ ውጭ በነበረው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ የተገኙት።

ደጋፊዎቻቸው የተለመደውን "አራት ተጨማሪ አመታትን ይምሩ" በማለት የዘመሩላቸው ሲሆን ፤ በዝግጅቱ ላይ የተገኙትም ደጋፊዎች ሙቀታቸው እየተለካና ጭምብል እየተሰጣቸው ወደተዘጋጀው ቦታ አቅንተዋል።

ደጋፊዎቻቸው ፕሬዚዳንቱ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ወቅት በመምጣታቸው ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተጠቃችው አሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 7.8 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን 216 ሺህ ዜጎቿንም መነጠቋን ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።