አፍጋኒስታን፡ ጉዳት የደረሰባቸውን የአፍጋኒስታን ወታደሮችን የጫኑ ሄሊኮፕተሮች ተጋጩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የተጎዱ የአፍጋኒስታን ወታደሮችን ጭነው ሲበሩ የነበሩ ሁለት ሄሊኮፕተሮች በደቡብ ሄልማንድ አውራጃ ተጋጭተው ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ።
የሞቱት ወታደሮች በአጠቃላይ በሄሊኮፕተሩ ውስጥ የነበሩ ናቸው ተብሏል።
ዕሮብ ማለዳ የደረሰው ይህ አደጋ የተከሰተው በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ነው ተብሏል።
በአካባቢው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታሊባን ታጣቂዎች እና በአሜሪካ መንግሥት በሚታገዘው የአፍጋኒስታን መንግሥት ወታደሮች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው በግጭቱ ምክንያት ከ35 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለዋል ተሰድደዋል።
በታሊባን ታጣቂዎችና በመንግሥት መካከል የሰላም ስምምነት ከደረሰ በኋላ የተደረገ ከባዱ ጦርነት መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአፍጋኒስታን የሚገኘው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ኃላፊ፣ የአሜሪካ ጦር ጄነራል ስኮት ሚለር ታሊባን የሰላም ስምምነቱን በመጣሱ እና ከአሜሪካ ጋር በየካቲት ወር የተፈረመውን ስምምነት በመተላለፉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ውጊያው እየተካሄደ የሚገኝበት የሄልማንድ እና ካንዳራ አካባቢ መንደሮች ታሊባን ታጣቂዎች ሰኞ ዕለት የመብራት ኃይል ማከፋፈያውን ካጠቁ ወዲህ መብራት ተቋርጦባቸዋል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው የስልክ ግንኙነት መስመሮችም ጥቃት ደርሶባቸዋል።
















