አፍጋኒስታን ውስጥ አይ ኤስ ባደረሰው ጥቃት 29 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) በአፍጋኒስታን እስር ቤት ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን እወስዳለሁ አለ።
ጥቃቱ የጀመረው እሁድ ምሽት የእስር ቤቱ መግቢያ በር ላይ ታጣቂዎች መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ከፈነዳ በኋላ ነበር።
በጥቃቱ ከ29 ያላነሱ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሞክረዋል።
አይኤስ ያደረሰው ጥቃት ከእሁድ ምሽት እስከ ሰኞ ንጋት ድረስ ዘልቆ የቆየ ሲሆን፤ የአፍጋኒስታን መንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ከታጣቂዎች ጋር ሲዋጉ ነበር።
ጥቃቱ የተሰነዘረበት እስር ቤት ከ1700 በላይ ታሳሪዎች እንደሚገኙበት እና ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ የታሊባን እና የአይኤስ ታጣቂዎች መሆናቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
እንደ ግዛቱ አስተዳዳሪ ቃል አቀባይ ከሆነ 1,025 ያመለጡ እስረኞች መመለስ የተቻለ ሲሆን 430 ያህሉን ደግሞ ማዳን ተችሏል። በጥቃቱ 50 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል።
እስካሁን ድረስ ምን ያህል እስረተኞች እንዳመለጡና እንዳልተያዙ የተባለ ነገር የሌለ ሲሆን ምን ያህል እንደሞቱም አልተገለፀም።
በእስር ቤቱ ላይ የደረሰው ጥቃት ታጣቂዎቹን ለማስመለጥ ያለመ ስለመሆኑ እስካሁን ድረስ አልተረጋገጠም።
በጥቃቱ ወቅት እስረኞች ከእስር ቤት ስለማምለጣቸው የተባለ ነገር የለም።
ጥቃቱ የተሰነዘረው በአፍጋኒስታን እና ታሊባን መካከል ለሦስት ቀናት የሚዘልቅ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ከመጠናቀቁ በፊት ነበር።
ሁለቱ ወገኖች ወደ ሰላማዊ ድርድር ለመመለስ ሲባል በመቶዎች የሚቆጠሩ የታሊባን እስረኞች እንዲፈቱ ተደርጓል።
ታሊባን ቀደም ሲል በእስር ቤቱ ላይ ለደረሰው ጥቃት እጄ የለበትም ብሎ ነበር።
















