ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስያ፡ የሲንጋፖር አየር መንገድ የቆሙ አውሮፕላኖቹን ምግብ ቤት አደረገ
ሲንጋፖራውያን ምሳቸውን ለመመገብ ወደ አየር መንገድ ጎራ ብለው አንድ ጥግ የቆመ A380 ኤርባስ አውሮፕላን ውስጥ መሰየም ብቻ ይጠበቅባቸዋል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ ምሳቸውን ለመመገብ የቋመጡ ሰዎች ለሁለት ቀን የተዘጋጀውን ወንበር ሙሉ በሙሉ ይዘውታል።
በዚህ አውሮፕላን ውስጥ ገብቶ ለመመገብ 496 የአሜሪካ ዶላር መክፈል ይጠበቃል።
አየር መንገዱ አገልግሎቱን ፈላጊዎች ስለበዙበት ሁለት ተጨማሪ ቀናትን ምሳና እናት ለማስተናገድ በማሰብ መጨመሩን አስታውቋል።
የሲንጋፖር አየር መንገድ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ገበያ አጥተው ፈተና ውስጥ ከወደቁ እና ሌሎች አማራጭ ከሚፈልጉ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ነው።
አየር መንገዱ በአሁን ሰዓት ሁለት A380 ኤር ባስ አውሮፕላኖችን ለሶስት ሰዓት የምግብ መስተንግዶ እንዲሰጡ ለመጠቀም አቅዷል።
ሁለቱም አውሮፕላኖች አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ በሚያስችል መልኩ ተደራጅተው በግማሽ አቅማቸው ብቻ ደንበኞችን ያስተናግዳሉ።
ተመጋቢዎች እየተመገቡ ፊልም መመልከት ቢፈልጉ ወይንም ደግሞ በምቾት በተንቆጠቆተው ክፍል ውስጥ መስተናገድ ከፈለጉ መምረጥ ይችላሉ ተብሏል።
አውሮፕላኑ ግን ተመጋቢዎቹን ጭኖ መሬት ለቅቆ አይበርም ተብሏል።
የሲንጋፖር አየር መንገድ ምግቦቹን ፍላጎት ላላቸው ቤታቸው ድረስ እንደሚያቀርብ አስታውቋል። ይህ ደግሞ የአየር መንገዱ የጥንቃቄ ኪቶችንና የጠረጴዛ ሽፋኖች ያካትታል።
የሲንጋፖር አየር መንገድ በኮቪድ-19 ከተጎዱ የአየር መንገዶች መካከል አንዱ ነው
ባለፈው ወር አየር መንገዱ 4300 ሰራተኞቹን እንደሚያሰናብት ገልጾ ነበር።
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበርም በሺዎች የሚቆጠሩ የአቪየሽኑ ስራዎች በኮቪድ-19 ምከንያት እንደሚጎዱ አስጠንቅቆ ነበር።
290 አየር መንገዶችን የሚወክለው ይህ ተቋም በረራዎችን ከባለፈው አመት ጋር በማነጻጸር በ 66 በመቶ ቀንሷል ብሏል።