ኮሮናቫይረስ፡ የቻይናዋ ከተማ በአምስት ቀናት ዘጠኝ ሚሊየን ነዋሪዎቿን ልትመረምር ነው

ታትሟል

የቻይናዋ ከተማ ኪንግዳዎ በሚቀጥሉት አምስት ቀናት 9 ሚሊየን የሚሆኑትን ሁሉም ነዋሪዎቿን የኮሮረናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ስራዋን ጀምራለች።

ለከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ ምርመራ ማድረግ ያስፈለገው በአንድ የኮሮረናቫይረስ ህሙማን በሚታከሙበት ሆስፒታል ውስጥ በአስርታት የሚቆጠሩ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

ባለፈው ግንቦት ወር ላይ የቻይናዋ ዉሀን ከተማ 11 ሚሊዮን ለሚሆኑ ነዋሪዎቿ በሙሉ ምርመራ ማድረጓ የሚታወስ ነው።

ቻይና በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ችላለች።

ይህ የሚባለው ግን ሌሎች ያደጉ አገራት ቫይረሱን በመቆጣጠር ረገድ ያሉበትን ደረጃ በመመልከትና አገሪቱ ካላት የህዝብ ቁጥር አንጻር እንጂ የቫይረሱ ስርጭት ቆሟል ማለት አይደለም።

በቻይናው ማህበራዊ ሚዲያ 'ዌቦ' በተለቀቀ መግለጫ ላይ የኪንግዳዎ ከተማ አስተዳደር ጤና ኮሚሽን ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አስታውቋል።

ግሎባል ታይምስ እንደዘገበው ደግሞ ሁሉም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ከአንድ ሆስፒታል ጋር ግንኙነት አላቸው።

ኮሚሽኑ አክሎም አጠቃላይ ምርምራ እንደሚደረግ በመግለጽ አምስት የከተማዋ ክፍሎች በመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት የሚሸፈኑ ሲሆን ሙሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ በአምስት ቀናት ውስጥ ምርመራ ይደረግላቸዋል ብሏል።

በማህበራዊ ሚዲያው እየተሰራጩ ባሉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ ከትናንት ጀምሮ በርካታ ነዋሪዎች ምርመራውን ለማድረግ ተሰልፈው የታዩ ሲሆን ምርመራው ከጠዋቱ አንድ ሰአት ጀምሮ ነው መከናወን የጀመረው።

የኪንግዳዎ ከተማ ጎረቤት የሆነችው ጂናን ደግሞ ለጉብኝትም ሆነ ለቤተሰብ ጥየቃ ወደ ኪንግዳዎ ሄደው የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች የኮሮረናቫይረስ ምርምራ እንዲያደርጉ አሳስባለች።

በአጠቃላይ ቻይና እስካሁን ድረስ 85 ሺ 578 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ 4634 ነው።