ኮሮናቫይረስ ፡ ቢሲጂ የተባለው የቲቢ ክትባት ከኮቪድ -19 ይታደገን ይሆን?

ታትሟል

በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ተመራማሪዎች እአአ በ1921 የተሰራው ቢሲጂ ክትባት ሰዎችን ከኮቪድ-19 ይታደግ እንደሆነ ለማወቅ ሙከራ ማካሄድ ጀምረዋል።

ባሲለስ ካልሜት ጉሪን (ቢሲጂ) የተባለው ክትባት የተሰራው የቲቢ በሽታን ለመከላከል ነበር። ይሁን እንጂ ክትባቱ ከሌሎች በሽታዎችም ሊጠብቅ እንደሚችል አንዳንድ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በኤክስተር ዩኒቨርሲቲ በሚካሄደው በዚህ የክትባቱ ሙከራ ላይ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሏል።

ምንም እንኳን በዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ህፃን ሳሉ ክትባቱን ቢወስዱም፤ ይህንን ጥቅም ለማግኘት በድጋሚ መከተብ አለባቸው የሚል ሃሳብ አለ።

ክትባቶች የሚሰሩት የሆነ በሽታን ለመከላከል የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓትን ለማለማመድ ነው።

ይህ ሂደት በሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት ውስጥ በርካታ ለውጦችን የሚያስከትል ሲሆን፤ ይህም ሰውነታችን ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል የሚሰጠውን ምላሽ ከፍ የሚያደረግ ነው።

ይህም ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለሰውነታችን አቅም ይሰጣል የሚል ተስፋን ለተመራማሪዎቹ ሰጥቷል።

• በክትባቱ ላይ ቀደም ብሎ የተሰራው ሙከራ ቢሲጂ ክትባት በጊኒ ቢሳዎ አዲስ የሚሞቱ ጨቅላ ህፃናትን ሞት በ38 በመቶ እንደቀነሰው አመላክቷል። ይህ የሆነው በአብዛኛው በሳንባ ምች እና ሴፕሲስ የሚከሰቱ ችግሮችን በይበልጥ በመቀነሱ ነው። ሴፕሲስ ሰውነት በሽታን ለመከላከል በሚሰጠው ከልክ ያለፈ ምላሽ ሳቢያ የሚከሰት ሲሆን፤ ህዋሳቶቻችን መጠቀም ከሚፈልጉት በላይ ኬሚካል በደም ባንቧዎቻችን በማመንጨት በበርካታ አካሎቻችን ሥራ ላይ እክል ያስከትላል።

• ከክትባቱ ጋር በተያያዘ በደቡብ አፍሪካ የተሰራው ጥናትም የአፍንጫ፣ የጉሮሮ እና የሳንባ ኢንፌክሽኖችን 73 በመቶ እንደቀነሰ ያሳያል። በኔዘርላንድስ የተሰራው ሙከራም በሰውነታችን ያለውን የቢጫ ወባ ቫይረስ መጠን እንደሚቀንስ አመልክቷል።

በኤክስተር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር ጆን ካምፕቤል "ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል፤ ነገር ግን አሁን ኮቪድ-19 ላይ ብቻ የተወሰነ ነው ብለን ባናስብም፤ ለኮቪድ-19 ክትባት ለማምጣት የሚወስደውን በርካታ ዓመታት ሊቀነስ ይችላል። ምን አልባት እስከዚያ ሌሎች መድኃኒቶችም ይበለፅጉ ይሆናል" ብለዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም እየተካሄደ ያለው ይሄው ሙከራ የዓለም አቀፉ ደጋፊ ጥናት አካል ሲሆን፤ በአውስትራሊያ፣ በኔዘርላንድስ፣ በስፔንና በብራዚል 10 ሺህ ሰዎችን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ ነው።

ጥናቱ በጤና እና በእንክብካቤ ሠራተኞች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ በእነርሱ ላይ ትኩረት መደረጉ ለኮሮናቫይረስ የመጋለጣቸው እድል ሰፊ በመሆኑ ነው።

ሰለዚህም ይህ ሙከራ ተመራማሪዎች ክትባቱ ውጤታማ መሆን አለመሆኑን በፍጥነት ለማወቅ ያስችላቸዋል ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በቢሲጂ ክትባት ላይ ላንሴት ለተባለው የህክምና መጽሔት ከፃፉ ሰዎች አንዱ ናቸው። በፅሁፋቸው ክትባቱ ለበሽታው ትክክለኛ ክትባት እስከሚበለፅግ ድረስ ያለውን ክፍተት እንደሚሞላ ገልፀዋል።

"ይህ ለኮቪድ -19 ለሚሰጠው ምላሽ እና ወደፊት ለሚከሰቱ ወረርሽኞች ጠቃሚ መሳሪያ ይሆናል" ይላል ፅሁፋቸው።

ይሁን እንጅ ቢሲጂ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ አይሆንም።

ክትባቱን በልጅነታቸው የተከተቡ ሰዎችም ዘላቂነት ባለው መልኩ በሽታውን መከላከል አይችሉም።

በዩናይትድ ኪንግደም የቲቢ በሽታ ደረጃ በመቀነሱ ከአውሮፓዊያኑ 2005 ወዲህ ክትባቱ በመደበኛነት ጥቅም ላይ አልዋለም።

ከዚህም በተጨማሪ ክትባቱ ኮሮናቫይረስን ለመለየትና ለመዋጋት አንቲቦዲና ነጭ የደም ሕዋስ ለማምረት የሰውነት የበሽታ መከላከል ሥርዓትን አያሰለጥንም።

በመሆኑም ዋናው ትኩረት ለኮሮናቫይረስ ብቻ የሚሆን ክትባት ማግኘት ሆኗል።

በዓለማችን እየበለፀጉ ካሉ ክትባቶች በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እየተሰራ ያለውን ጨምሮ አስሩ የመጨረሻ ደረጃ የክሊኒካል ሙከራ ላይ ናቸው።