ሙስና፡ ባለሥልጣናት የተዘፈቁበት ሙስና በደቡብ አፍሪካ

ታትሟል

ባሳለፍነው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሁለት ፎቶዎች መነጋገሪያ ሆነዋል። ስለ ሙስና እና የፍትሕ ሥርዓትን ለመጠገን የሚደረገው ጥረትም ጥያቄ አጭረዋል።

የመጀመሪያው ፎቶ የቅንጡ ፌራሪ እና ቤንትሊ መኪና እንዲሁም የሁለት ቪላ ቤቶች ነው። እነዚህና ሌሎችም ወደ 18.2 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚገመቱ ንብረቶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ሁለተኛው ፎቶ ደግሞ ሰንከል በተባለች ግዛት በጣም የተቆጡ አርሶ አደሮች በተቃውሞ አደባባይ ሲወጡና የፖሊስ መኪና ሲያቃጥሉ ያሳያል።

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ጄኮብ ዙማ ከሥልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ የመጡት መሪ፤ በጄኮብ ዘመን ተንሰራፍቶ የነበረውን ሙስና ለማስወገድ ቃል ገብተዋል።

ሕዝቡ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ተጠያቂ ሲደረጉ ለማየት ጓጉቷል። ዜጎች ትዕግስታቸው እስኪሟጠጥ ድረስ ኃላፊዎች ታስረው ሙስና የሚያከትምበትን ቀን ይጠብቃሉ።

ባለፈው ሳምንት ቅንጡ መኪኖችና ቪላ ቤቶች እገዳ ተጥሎባቸው ሰባት ነጋዴዎችና የመንግሥት ባለሥልጣኖች ታስረዋል። ክስም ተመስርቶባቸዋል።

ይህ የመንግሥት ኃላፊነትን መበጠቀም የሚከናወኑ ሕገ ወጥ ተግባሮች ማሳያ ነው። ነጋዴዎች ከባለሥልጣኖች ጋር ተመሳጥረው የግብር ከፋዩን ሕዝብ ሀብት ይመዘብራሉ።

ባለሥልጣኖች እና ሙስና

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የአገሪቱ ዓቃቤ ሕግ፤ ከአንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር እንደተደራደረና፤ ባለሥልጣኑ በሙስናው እጃቸው ያለበት ሰዎችን ለማጋለጥ እንደተስማሙ ይፋ አድርጓል።

ዓቃቤ ሕግ ከዚህ ቀደም በደቡብ አፍሪካ ታሪክ እጅግ የከፋ ከተባለው የሙስና ቅሌት ጋር በተያያዘ ስምንት ሰዎች ላይ ክስ መስርቷል።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ‘ዞንዶ ኮሚሽን’ የተባለ፣ በዳኛ የሚመራና የባለሥልጣኖች እጅ ያለበትን ሙስና የሚመረምር ቡድን ተቋቁሟል።

ይህ ቡድን ከዓቃቤ ሕግ ጋር በቅርበት ይሠራል። በሁለቱ ጥምረት አማካይነት የሙስና ቅሌቶች መጋለጣቸው፣ ተጠያቂዎቹም ለፍርድ መቅረባቸው የሕዝቡ ተስፋ እንዲያንሰራራ ምክንያት ሆኗል።

ገዢ ፓርቲው ኤኤንሲ፤ አዲስ የጸረ ሙስና ተቋም ለመመሥረት ቃል ገብቷል። ተቋሙ ከማንኛውም አይነት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ይሆናል ተብሎም ነበር።

ቀድሞ የነበረው የጸረ ሙስና ተቋም (ዘ ስኮርፒዮንስ) በዋናነት ይተች የነበረው በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነበር። ተቋሙ ባለሥልጣኖች ላይ ጫና ማሳደር ሲጀምር ከዓሥር ዓመት በፊት በምክር ቤት ውሳኔ ፈርሷል።

አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴ የፓርቲው ጸሐፊ ኤስ ማጋሹሌን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ መሪዎችን ነክቷል። ጸሐፊው ባለፈው ሳምንት ፖለቲካዊ እስር ሊፈጸምብኝ ነው ብለው ነበር።

የቀረቡባቸውን የሙስና ክሶች አጣጥለዋል።

አዲሷ ዓቃቤ ሕግ ሻሚላ ባቶህ “ቀድሞ እንዲህ አይነት ክሶች ፍርድ ቤት አይቀርቡም ነበር። ነገሮች እየተለወጡ ነው” ብለዋል።

ችግሩ ተቀርፏል?

ሰንከል በተባለች ግዛት በጣም የተቆጡ አርሶ አደሮች በተቃውሞ አደባባይ ሲወጡና የፖሊስ መኪና ሲያቃጥሉ የሚያሳየው ፎቶ፤ አሁንም የሲሪል ራማፎሳ አስተዳደር ውስጥ ያለው ችግር ገና እንዳልተቀረፈ ያሳያል ብለው የሚያምኑ ብዙ ናቸው።

አርሶ አደሮቹ የተቆጡት በአካባቢያቸው በተከሰተ ነገር ቢሆንም፤ በመላው ደቡብ አፍሪካ አሁንም ችግሮች እንዳሉ ማሳያ ነው።

በአካባቢው የ22 ዓመት ነጭ ግለሰብ ተገድሎ አስክሬኑ ፖል ላይ ተሰቅሏል።በአገሪቱ ሕገ ወጥነት መንሰራፋቱ፤ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት ላይ እምነት መጥፋቱም ይነገራል።

በተጨማሪም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

አዲሷ ዓቃቤ ሕግ ሻሚላ ባቶህ፤ “ገና ትግሉን አላሸነፍንም። በጣም ብዙ ሥራ ይቀረናል” ብለዋል።

ድርጅታቸው በቂ የሰው ኃይልና ሌሎችም ግብዓቶች እንዳጠሩትም አክለዋል።

“ሥርዓቱ ተሰብሯል ብቻ ሳይሆን በስብሷል። ሥራችንን ለማደናቀፍ የሚሞክሩም አሉ” ያሉት የምርመራ ክፍሉ ኃላፊ ሄርሞይም ክሮንጄ ናቸው።

አገሪቱን ከሙስና የማጽዳት ንቅናቄን የሚያደናቅፉ አካሎች አሉ መባሉ፤ ሂደቱ በተወሰነ ደረጃ ፖለቲካዊ መሆኑን ይጠቁማል።

የጸረ ሙስና ድርጅት የሆነው ‘አካውንተብሊቲ ናው’ አባል ፖል ሆፍማን “ዓቃቤ ሕግ አንድ እጁን ታስሮና አንድ ዓይኑ ተሸፍኖ ምንም አለማድረጉ የሚያስቃቸው ኃላፊዎች አሉ” ብለዋል።

በሙስና የተጠረጠረ ባለሥልጣን ከኃላፊነቱ ይነሳ? የሚለው የኤኤንሲ ውሳኔ ነው። ፕሬዘዳንት ራማፎሳ ይህን ማሳካት ከቻሉ የጸረ ሙስና ትግል ፍሬ ሊያፈራ ይችላል።

ሆኖም ግን ውሳኔዎች በፓርቲ ፖለቲካ ከተዋጡ እንደቀደመው የዙማ ዘመን ባለሥልጣኖች ከክስ ያመልጣሉ።

አገሪቱን ከሙስና ማጽዳት እያሽቆለቆለ ለመጣው ምጣኔ ሀብት መፍትሔ ይሰጣል? ሌለው ጥያቄ ነው።

ባለ ሀብቶች፣ ተንታኞችና ዲፕሎማቶችም ደቡብ አፍሪካ የእዳ ቀውስ ውስጥ እንደገባችና የኋላ ኋላ መንኮታኮቷ እንደማይቀር ይናገራሉ።

ነጋዴና የፖለቲካ ተንታኝ ሞልተሲ ምቤኪ እንደሚሉት፤ አገሪቱ ወደ ከፍተኛ ችግር እያመራች ነው።“ምጣኔ ሀብቱ መጠገን አለበት። ነገር ግን ኢንቨስትመንት የለም። ኤኤንሲ ምን እየመጣ እንደሆነ አልተገነዘበም” ብለዋል።