ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮቪድ-19፡ በብራዚል የሚሰጠው እርዳታ ከቆመ ሚሊዮኖች ለድህነት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ጥናት አመለከተ
በብራዚል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በየወሩ የሚሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ከቆመ፤ 15 ሚሊዮን ሰዎችን ለድህነት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አንድ ጥናት አመለከተ።
ወረርሽኙ ያሳደረውን ቀውስ ለመቀነስ፤ እስካሁን በአገሪቷ ከ67 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እርዳታውን ተቀብለዋል።
በዚህም ምክንያት 50 ሚሊዮን ሰዎች ከድህነት አዘቅት ወጥተዋል፤ ይህም በታሪኳ ዝቅተኛ አሃዝ መሆኑን ፈንዳቾ ጌቱሊዮ ቫርጋስ የተባለው የጥናት ተቋም ገልጿል።
መንግሥት የዚህ ፕሮግራም አካል ሆኖ መቀጠል ቢፈልግም መጠኑ ላይ ግን ጥያቄዎች ይነሳሉ።
የፕሬዚዳንት ጀር ቦልሶናሮ ጥረትም በምክር ቤቱ ተገትቷል። በአገሪቷ ባለው የበጀት ጉድለት ሳቢያ በተፈጠሩ ስጋቶች በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው በጀት መጠን ሳይጣስ፤ ፕሮግራሙን እንዴት እንደግፍ በሚለው ላይ በደጋፊዎቻቸው መካከልም አለመግባባት አለ።
የቁጠባ እና የተሃድሶ አጀንዳዎችን ይዘው ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዚዳንቱ፤ በሚያዚያ ወር ተጀምሮ በታህሳስ ወር የሚጠናቀቀው እርዳታ በማስተዋወቃቸው ዝነኝነታቸው ጨምሯል።
ይህ የገንዘብ ድጋፍ በነሐሴ ወር ላይ በግማሽ ከመቀነሱ በፊት በ107 ዶላር ነበር የተጀመረው።
በብራዚል አንድ ሰው ድሃ ነው የሚባለው ዝቅተኛ የቀን ገቢ ተብሎ ከተቀመጠው ግማሽ ወይም [93 ዶላር] በታች ካገኘ ነው።
ባለሥልጣናት እንዳሉት እስካሁን 44 በመቶ የሚሆኑት ብራዚላዊያን ቤተሰቦች ክፍያውን ተቀብለዋል። አብዛኞቹም በአገሪቷ የባሰ ድህነት ባለባቸው በሰሜናዊ እና ሰሜን ምስራቅ ግዛቶች የሚኖሩ ናቸው።
በጥናት ተቋሙ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ የሆኑት ማርሴሎ ኔሪ ፤ "15 ሚሊዮን ሰዎች ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ ተመልሰው እንደሚገቡ የተቀመጠው ግምት አነስተኛ ነው፤ ከዚህም ሊበልጥ ይችላል" ብለዋል።
"ብራዚል በቂ የገንዘብ በጀት ያላት አገር ባትሆንም፤ በላቲን አሜሪካ ካሉ አገራት ጥሩ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጥ ፕሮግራም የነበራት አገር ናት። ይህ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ለውጥ እንዳመጣ እናያለን" ብለዋል ባለሙያው።
በሌሎች የላቲን አሜሪካ አገሮች አንድ ሰው በከፋ ድህነት ውስጥ ነው የሚባለው ከ1.90 ዶላር በታች የቀን ገቢ ሲኖረው ነው።
በእነዚህ በወረርሽኙ ክፉኛ በተመቱት አገራት የድህነት ደረጃው እንዲሁም የከፋ ድህነቱ ሊያይል እንደሚችል ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በብራዚል የወረርሽኙ ሥርጭት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እየቀነሰ ነው። ሱቆችና ሌሎች የንግድ ተቋማት እንደገና እየተከፈቱ ነው።
ይሁን እንጅ አገሪቷ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድቀት ሊገጥማት ስለሚችል የሥራ አጥ ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አለ።
212 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ያላት ብራዚል በቫይረሱ ክፉኛ ከተመቱ የዓለማችን አገራት አንዷ ናት።
እንደ የአገሪቷ ጤና ሚኒስቴር መረጃም እስካሁን 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ወደ 149 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችም በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።
መረጃው እንደሚያመለክተው ሴቶችና ጥቁሮች በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቁ ሕብረተሰብ ክፍሎች ናቸው።
በኮሮናቫይረስ ተይዘው ያገገሙት ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ፤ ለወረርሽኙ በሰጡት ምላሽ በስፋት ይተቻሉ። መጀመሪያ አካባቢም "ቀላል ጉንፋን ማለት ነው" እያሉ ቫይረሱን ያጣጥሉ ነበር።
አካላዊ ርቀትን እንደመጠበቅ ያሉ በጤና ባለሙያዎች የተሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችንም ይቃወሙ ነበር።