ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮቪድ-19፡ ሲንጋፖር የሚወለዱ ሕፃናትን ቁጥር ለመጨመር የገንዘብ ጉርሻ ልትሰጥ ነው
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያላናጋው ነገር የለም። ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተጣሉት ገደቦችም በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊው፣ በሥነ ልቦና እንዲሁም በፖለቲካው ዘርፍ በርካታ ተፅዕኖዎችን አሳድረዋል።
የደቡብ ምስራቅ እስያዊቷ አገር ሲንጋፖርም ወረርሽኙ በሌላው ዘርፍ ላይ ካሳደረው ጉዳት ባለፈ ዜጎቼ 'ዐይናቸውን በዐይናቸው' እንዳያዩ አድርጎብኛል ብላለች።
በወረርሽኙ ሳቢያ በገንዘብና በሥራ ማጣት ምክንያት ዜጎቿ መውለዳቸውን እየተውት አሊያም እያዘገዩት መሆኑ አሳስቧታል።
በመሆኑም እንዲወልዱ ለማበረታታት በአንድ ጊዜ የሚከፈል የገንዘብ ጉርሻ ልትሰጥ መሆኑን ገልፃለች።
የሚሰጣቸው የገንዘብ መጠን ዝርዝር ይፋ ባይደረግም፤ መንግሥት ከዚህ ቀደም ለህፃናት ከሚሰጠው ከፍተኛ ጉርሻ ጭማሪ ነው ተብሏል።
የአገሪቷ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንግ ስዌ ኬት "በኮቪድ-19 ወረርሽኙ ሳቢያ በርካታ ወላጆች ልጅ የመውለድ እቅዳቸውን እንዳራዘሙት መረጃዎች ደርሰውናል" ብለዋል።
የገንዘብ ድጎማውን ለመስጠት የተወሰነውም ይህንን ተከትሎ ነው።
ሚኒስትሩ ወላጆች እንዲወልዱ ለማበረታት የሚሰጠው የገንዘብ ጉርሻ መጠንና የአከፋፈሉ ሥርዓት በቀጣዩ ቀን እንደሚገለፅ ተናግረዋል።
ሲንጋፖር በዓለማችን ዝቅተኛው የውልደት መጠን ካለቸው አገራት መካከል አንዷ ናት። ይህንንም ለማሳደግ ላለፉት አስርት ዓመታት ስትታገል ቆይታለች።
በአገሪቷ ተግባራዊ እየሆነ ባለው የገንዘብ ጉርሻ ሥርዓት ልጅ ለመውለድ ብቁ ለሆኑ ወላጆች በአጠቃላይ እስከ 10 ሺህ ዶላር ጥቅማ ጥቅም ትሰጣለች።
ሁኔታው ከሌሎች ጎረቤት አገሮቿ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ተቃራኒ ነው።
በጎረቤት አገሮቿ ኢንዶኔዥያና ፊሊፒንስ በወረርሽኙ ወቅት የተጣለውን ቤት የመቀመጥ ገደብ ተከትሎ ከፍተኛ የነፍሰጡሮች ቁጥር ጨምሯል።
ይህ ዜና ግን ለሲንጋፖር ሩቅ ይመስላል።
መንግሥት ባወጣው መረጃ መሰረት የሲንጋፖር የውልደት መጠን እአአ በ2018 የ8 ዓመታት ዝቅተኛው ቁጥር ተመዝግቧል። በአማካይ አንዲት ሴት 1.14 ህፃናትን እንደምትወልድም መረጃው አመልክቷል።
አብዛኞቹ የእስያ አገራት የውልደት ቁጥር መቀነስ ችግር ያጋጥማቸዋል። ይህ ደግሞ በወረርሽኙ ሳቢያ ተባብሶ ታይቷል።