ኮሮናቫይረስ፡አማዞን ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞቹ በኮሮና እንደተያዙ አስታወቀ

ታትሟል

አማዞን ኩባንያ 19 ሺህ 816 ሰራተኞቹ በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ ገልጿል።

ይህ ቁጥር ከመጋቢት ወር ጀምሮ የተመዘገበ ሲሆን በአሜሪካ ያሉት ሰራተኞቹም ናቸው።

በአጠቃላይ ኩባንያው 1.37 ሚሊዮን ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በኮሮናቫይረስ የተያዙትም ከአጠቃላይ ሰራተኞቹ ቁጥር ጋር ሲሰላ 1.44 በመቶ ነው ተብሏል።

የኩባንያው ሰራተኞች፣ የሰራተኛ ማህበራትና ኃላፊዎችም የሰራተኞችን ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል በሚልም ኩባንያው ከፍተኛ ትችት እየቀረበበት ነው።

ሆኖም ኩባንያው በበኩሉ በቫይረሱ የተያዙት ሰራተኞች ቁጥር ከተጠበቀው በታች ነው ብሏል።

ኩባንያው ባወጣው መግለጫም በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ከግምት ውሰት በማስገባት 33 ሺህ 952 ሰራተኞቹ በቫይረሱ እንደሚያዙ ጠብቆ እንደነበር አስታውቋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በርካታ ኩባንያዎች ለተወሰነ ጊዜ ስራቸውን ቢያቆሙም አማዞን በበኩሉ የትኞቹንም ቅርንጫፎች አልዘጋም።

በዚህ ወረርሽኝ ወቅትም ትርፋማ ከሆኑት ኩባንያዎች አንዱ መሆን ችሏል።

አገራት ወረርሽኙን ለመግታት በሚል ያወጧቸውን መመሪያዎች ተከትሎ በርካቶች ቤታቸው በመቀመጣቸው የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ግብይይት ሁነኛ አማራጭ ሆኗል።

ይህም ሁኔታ ለግዙፉ ኩባንያ አማዞንና በአለም አንደኛ ለሆነው ባለቤቱ ጄፍ ቤዞ በትርፍ ላይ ትርፍ ሆኖለታል።

በባለፉት ሶሰት ወራትም ውስጥ ኩባንያው 40 በመቶ ሽያጩ ጨምሯል። ከመጋቢት እስከ ሰኔ ወራት ባሉትም 88.9 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭን ሲያስመዘግብ፣ ከዚህም ውስጥ 5.2 ቢሊዮን ዶላሩ ትርፍ ነው።

ኩባንያው ከተመሰረተበት ከጎሮጎሳውያኑ 1994 ጀምሮም እንዲህ አይነት ትርፍ አስመዝግቦ አያውቅምም ተብሏል።