ኮሮናቫይረስ፡ ኬንያ መጠጥ ቤቶች እንዲከፈቱ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንዲቆዩ ወሰነች

ታትሟል

ኬንያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ላለፉት ስድስት ወራት ዝግ ሆነው የቆዩት የአልኮል መጠጥ የሚሸጥባቸው የምሽት መዝናኛ ቤቶች ከማክሰኞ ጀምሮ እንዲከፈቱ ተወሰነች።

ይሁን እንጂ መስራት የሚችሉት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ብቻ ነው ተብሏል።

ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ሰኞ በሰጡት መግለጫ መንግሥት ወረርሽኙን ለመግታት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ፕሬዚደንቱ በመግለጫቸው በአገሪቷ የተጣለው የሰዓት እላፊ ለሁለት ወራት ያህል መራዘሙን የገለፁ ሲሆን፤ የሰዓት እላፊው ግን ከምሽቱ 5 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ድረስ እንዲቆይ ሆኖ መሻሻሉን አስታውቀዋል።

የተደረገው የሰዓት ማሻሻያም ከነገ ማክሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

በሌላ በኩል በርካቶች ሲጠብቁት የነበረው የትምህርት ቤቶች መከፈት ጉዳይ ላይ የተደረገ ለውጥ ሳይኖር ቀርቷል።

የትምህርት ሚኒስቴር መምህራን ሰኞ ዕለት በየትምህርት ቤታቸው ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ቢያቀርብም፤ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ግን ትምህርት ቤቶች መከፈት የሚችሉት የተማሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ሲቻል ነው ብለዋል።

በኬንያ እስካሁን ከ38 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ሕይወታቸው ያለፉትን 9 ሰዎች ጨምሮ በአጠቃላይ ከ700 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአገሪቷ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ግን እየቀነሰ ነው። ሰኞ ዕለት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 53 ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ ይህ የሆነው የአገሪቷ የምርመራ ቁጥር ዝቅተኛ በመሆኑ ነው የሚል ትችት ይቀርብባታል።