በኢንግላንድ ኮኖናቫይረስ የሚመረመሩ ልጆች ቁጥር ጨምሯል

ታትሟል

ኮሮናቫይረስ በዋነኛነት የሚጎዳው አረጋውያንን መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሕፃናት ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ ግን አልቀረም።

ኢንግላንድን እንደ ማሳያ ብንወስድ በአገሪቱ የኮቮድ-19 ምርመራ የሚያደርጉ ልጆች ቁጥር በዚህ ወር ጨምሯል።

ከተመረመሩት መካከል አንድ በመቶው ብቻ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

በመጀመሪያዎቹ የመስከረም ሳምንታት ከ200,000 በላይ እድሜያቸው ከዘጠኝ ዓመት በታች የሆነ ታዳጊዎች ተመርምረዋል።

ይህም ካለፉት ወራት አንጻር ሦስት እጥፍ ይሆናል።

ጥናት እንደሚያሳየው ልጆች ከአዋቂዎች አንጻር ለበሽታው የመጋለጥ እድላቸው ጠባብ ነው። ሆኖም ግን ሕፃናት በሽታውን ያስተላልፋሉ? ለሚለው ጥያቄ አሁንም ቁርጥ መልስ አልተገኘም።

የኢንግላንድ አሃዝ እንደሚጠቁመው፤ ምርመራ የሚያደርጉ ከ40 ዓመት በታች ያሉ ግለሰቦች ቁጥር ጨምሯል። አብላጫውን ድርሻ የሚይዙት በ20ዎቹ እድሜ ክልል ያሉት ናቸው።

ምርመራ የሚያደርጉ ልጆች ቁጥር የጨመረው ኢንግላንድ ውስጥ ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በመጀመሩ ነው። የተመርማሪዎች ቁጥር መናር የቤተ ሙከራ ውጤት እንዲዘገይ አድርጓል።

ከሚመረመሩት ታዳጊዎች መካከል ኮቪድ-19 የሚገኝባቸው አንድ በመቶው ብቻ ናቸው። በሌላ በኩል ከጎልማሶች 3.5% ቫይረሱ ይገኝባቸዋል። ይህ ቁጥር በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ እድሜ ክልል ያሉትንም ያካትታል።

ለምን የሚመረመሩ ልጆች ቁጥር ጨመረ?

የብርድ እንዲሁም ጉንፋን ምልክት የሚያሳዩ ልጆች ከሌሎች ታዳጊዎች ጋር መቀላቀል ጀምረዋል።

ኢንግላንድ ወደ ቀዝቃዛ ወቅት እየገባቸው እንደመሆኗ የተለያዩ የመተንፈሻ አካሎች ህመሞች ይቀሰቀሳሉ። የእነዚህ በሽታዎች ምልክት ደግሞ ከኮሮናቫይረስ ጋር ተቀራራቢ ነው።

ስለዚህም የኮሮናቫይረስ ምርመራ የሚያደርጉ ልጆች ቁጥር ንሯል።

በእርግጥ ልጆች በቫይረሱ ቢያዙም በጠና አይታመሙም።

ጃማ ፔዲያትሪክስ የሚባለው የዩናይትድ ኪንግደም የጥናት ቡድን ከ20 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች ለወረርሽኙ የመጋለጥ እድላቸው 44% ነው።

በተለይም ከዓሥር ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት እምብዛም ለበሽታው አይጋለጡም።

ቡድኑ ከምሥራቅ እስያ፣ አውሮፓና ሌሎችም የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ 21 አገሮች ውስጥ የተካሄደ ጥናትን ዳሷል። በጥናቱ 42,000 ሕጻናት እና 270,000 አዋቂዎች ተሳትፈዋል።

ጥናቱ ልጆች በሽታውን ወደ ሌላ ሰው ያስተላልፋሉ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።

ልጆች በበሽታው ከተያዙ ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። ሳል ከሌላቸው ወይም በጠና ካልታመሙ ምናልባትም በሽታውን አያስተላልፉ ይሆናል የሚል መላ ምት አለ።

ስለዚህም በሽታውን የማሰራጨት መጠን ምን ያህል ለበሽታው ተጋልጠዋል? ምን ያህል ቫይረስ ተሸክመዋል? ከምን ያህል ሰዎች ጋር ንክኪ አላቸው? በሚሉት ጥያቄዎች ይወሰናል።

ቫይረሱ በልጆችና በጎልማሶች ምን ያህል እንደተሰራጨ ለማወቅ በበሽታው ከተያዙ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ላይ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያስፈልግ አጥኚዎቹ ጠቁመዋል።