በአሜሪካ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200ሺህ ተሻገረ

ታትሟል

በአሜሪካ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ከ200ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው አሐዝ ጠቆመ።

በአሜሪካ ከ6.8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በኮሮናቫይረስ የተያዝ ሲሆን ይህም ከየትኛውም አገር በላይ ነው።

በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ200ሺህ መሻገሩ የተሰማው በአገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ስለመሆኑ ሪፖርት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።

የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየጨመረ በመጣበት ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ፕሬዝደንት ትራምፕ በአሜሪካ በቫይረሱ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ100ሺህ እስከ 200ሺህ መካከል ከሆነ በሽታውን የመከላከላችን ሥራ ውጤታማ ሆኗል ማለት ነው ብለው ነበር።

በአሜሪካ ጥቅምት ወር ላይ በቫይረሱ የተያዙ 15 ሰዎች በተገኙ ወቅት ትራምፕ “በቀጣዮች ቀናት ቁጥሩ ወደ ዜሮ ይጠጋል” ብለው ነበር።

ዛሬ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሐዝ እንደሚጠቁመው ከሆነ እስካሁን ድረስ በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 200 ሺህ 005 ነው።

የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በወሰደው ደካማ እርምጃ ትችቶች ይቀርቡበታል።

“በዶናልድ ትራምፕ ውሸት እና የአመራር ብቃት ማነስ ምክንያት ባለፉት ስድስት ወራት የበርካታ አሜሪካውያን ሞትን ተመልክተናል” ሲሉ የዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኝ ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት የአሜሪካ ግዛቶች ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየመዘገቡ ይገኛሉ።

የሰሜን ዳኮታ ግዛት አስተዳዳሪዎች ከ3200 በላይ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በዩታህ፣ ዊስኮንሲን፣ ቴክሳስ እና ደቡብ ዳኮታ ግዛቶችም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

መጪው የፈረንጆቹ የክረምት ወቅት የቅዝቃዜው መጠን ስለሚጨምርና ለቫይረሱ ስርጭት አመቺ ስለሚሆን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዳይንር ተሰግቷል።