የትራምፕ አስተዳደር ዊቻትን እንዳያግድ ፍርድ ቤት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቻይናውን መተግበሪያ ዊቻት አሜሪካ ለማገድ ያደረገችውን ጥረት ፍርድ ቤት አስቆመ።
ዳኛ ሎረል ቤለር፤ አሜሪካ ዊቻትን ለማገድ መሞከሯ ሕገ መንግሥቱ የደነገገውን የንግግር ነጻነትን ይጻረራል ብለዋል።
የአሜሪካ የንግድ ተቋም፤ ዊቻት በአገሪቱ የመተግበሪያ መጫኛዎች ላይ እንዳይገኝ ውሳኔ አስተላልፏል።
ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፐ መተግበሪያው ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው ብለዋል። መተግበሪያው የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ ለቻይና መንግሥት አስተላልፎ ይሰጣል ሲሉም ተደምጠዋል።
ቻይና እና የዊቻት ድርጅትም ክሱን አጣጥለዋል። ዊቻትን የሚያስተዳድረው ቴንሴንት አሜሪካ መተግበሪያውን ለማገድ ማሰቧ አሳዛኝ ነው ብሏል።
ውሳኔው የተላለፈው ቲክቶክ ሥራውን መቀጠል እንዲችል ከአሜሪካዎቹ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ኦራክል እና ዋልማርት ጋር ከተስማማ በኋላ ነው።
ትራምፕ ዊቻትን ለማገድ ሲወስኑ፤ አሜሪካ የሚገኙ የዊቻት ተጠቃሚዎች ክስ መስርተዋል።
የአሜሪካ የፍትሕ ተቋም የትራምፕን ውሳኔ ማገድ ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ትግል ያደናቅፋል ብሏል።
ሆኖም ግን የሳን ፍራንሲስኮው ዳኛ “ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሆኑ የቻይና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በተመለከተ የቀረበው ማስረጃ የሚያስኬድ ቢሆንም ስለ ዊቻት ግን የተሟላ ማስረጃ አልቀረበም” ብለዋል።
አሜሪካ ለምን መተግበሪያውን ማገድ ፈለገች?
የአገሪቱ የንግድ ተቋም ጸሐፊ ዊበር ሮስ፤ መተግበሪያውን ለማገድ የተወሰነው ቻይና የአሜሪካውያንን የግል መረጃ እንዳትሰልል ነው።
ዊቻት ተጠቃሚዎች ያሉበትን ቦታ፣ የሚጠቀሙትን ኔትወርክ፣ የኢንተርኔት አሰሳቸውን እንዲሁም ሌሎችም የግል መረጃዎች እየሰበሰበ ነው ሲል ተቋሙ ይከሳል።
መተግበሪያው የአሜሪካን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚከት፣ ለውጪ ግንኙነት ፖሊሲ እና ምጣኔ ሀብት ስጋት የሆነ ነው ሲልም ተቋሙ መግለጫ አውጥቷል።
ቴንሴንት በበኩሉ ዊቻት ላይ ሰዎች የሚለዋወጧቸው መልዕክቶች ሚስጥራዊ ናቸው ይላል።
አሜሪካ ውስጥ ወደ 20 ሚሊዮን የዊቻት ተጠቃሚዎች አሉ። ከነዚህ መካከል የቻይና እና የደቡብ ምሥራቅ እስያ ተወላጆች ይገኙበታል።
ዊቻት ላይ እገዳ ከተጣለ በርካቶች ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚቸገሩ ይናገራሉ።
መተግበሪያው እአአ 2011 ላይ ነበር ሥራ የጀመረው። በዊቻት መልዕክት መለዋወጥ፣ ክፍያ መፈጸምና ሌሎችም ክንውኖች ማካሄድ ይቻላል።
ቻይና ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፤ በርካታ እንቅስቃሴዎች ዊቻትን የተመረኮዙ ናቸው።
እንደ ሌሎቹ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ዊቻትም መንግሥት ሕገ ወጥ የሚላቸውን ይዘቶች ሳንሱር ያደርጋል።
ዊቻት ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ቁልፍ ቃላትን ሳንሱር እያደረገ ነው መባሉ ይታወሳል።
ዊቻት እንደሚለው ከሆነ፤ የሰዎችን የግል መልዕክት ሦስተኛ ወገን ማግኘት አይችልም። የጽሑፍ፣ የድምጽና የምስል መልዕክት ተጠቃሚዎች ጋር ከደረሰ በኋላ መረጃው ይደመሰሳል እንጂ በሰርቨሩ አይከማችም።
















