ዶናልድ ትራምፕ፡ አሜሪካ ቲክ ቶክንና ዊቻትን በ48 ሰዓታት ውስጥ ለማገድ መዘጋጀቷን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Alamy/EPA/Alamy
ፕሬዚደንት ትራምፕ በመጨረሻው ሰዓት ሃሳባቸውን ካልለወጡ በስተቀር የቻይናዎቹን ቲክቶክና ዊቻት ከመጭው እሁድ ጀምሮ በአሜሪካ እንደሚታገዱ ተገለፀ።
የአሜሪካ የንግድ መሥሪያ ቤት፤ የአገሪቷ ዜጎች የዊቻት እና ቲክቶክ መተግበሪያዎችን እንዳያወርዱ ለማገድ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል የተናገረው አርብ ዕለት ነው።
ትዕዛዙ መተግበሪያዎቹ ከማንኛውም 'አፕስቶር' በማንኛውም መልኩ እንዳይሰራጩ ይከለክላል።
መንግሥት ባለቤትነታቸው የቻይና የሆኑት መተግበሪያዎች ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ መግለፁ ይታወቃል።
ይሁን እንጅ በአሜሪካው የኮምፒዩተር ኩባንያ ኦራክል እና የቲክቶክ ባለቤት የቻይናው ቴክኖሎጂ ኩባንያ ቢይቴዳንስ ከተስማሙና ስምምነቱ በፕሬዚደንት ትራምፕ ከፀደቀ መተግበሪያዎቹ ላይታገዱ ይችላሉ ተብሏል።
ፕሬዚደንት ትራምፕ "ሊያፀድቁት ይችሉ ይሁን አይሁን" ግልፅ የሆነ ነገር ባይኖርም፤ ቀነ ገደቡ ከመድረሱ በፊት ስምምነቱን እንደገና ያዩታል ተብሎ ይጠበቃል።
የንግድ መሥሪያ ቤቱ የእገዳ ትዕዛዙን ያወጣው ፕሬዚደንት ትራምፕ ነሐሴ ወር ላይ መተግበሪያዎቹ እንዲታገዱ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።
የንግድ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ ኃላፊው ዊልበር ሮስ " ፕሬዚደንቱ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት፤ ቻይና ከአሜሪካ ዜጎች ግላዊ መረጃ መበርበሯን ለመከላከል ስንል ተገቢውን እርምጃ ወስደናል" ብለዋል።
መሥሪያ ቤቱ በዊቻት እና ቲክቶክ የሚደርሰው የደህንነት አደጋ ተመሳሳይ አለመሆኑን ጠቅሶ፤ መተግበሪያዎቹ የተጠቃሚዎችን የኔትወርክ እንቅስቃሴን፣ የመገኛን [ሎኬሽን] ፣ የፍለጋ ታሪኮችን [ ሰርች ሂስትሪ] የተመለከቱ በርካታ መረጃዎች ሰብስበዋል ብሏል።
ይሁን እንጂ የቻይናው ኩባንያ ቢይቴዳንስ፤ የመረጃ ቋቱ በአሜሪካና በሲንጋፖር እንደሚገኙ በመግለፅ በቻይና የማንኛውንም ተጠቃሚ መረጃ ተበርብሯል መባሉን ተቃውሟል።
የዊቻት ባለቤት ቴንሴት በበኩሉ በመተግበሪያው ላይ ያሉ መልዕክቶች ደህንነታቸው የተጠበቀና ግላዊ ናቸው ብለዋል።
ቲክቶክ በአሜሪካ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፤ በቢሊዮን ከሚቆጠሩ የዊቻት ተጠቃሚዎች ከቻይና ውጭ የሚገኙት ምን ያህሉ እንደሆኑ ግን በግልፅ አይታወቅም።
ነገር ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተጠቃሚ እንደሚኖራቸው ይገመታል።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ቲክቶክ የተሰኘው ተንቀሳቃሽ ምስሎች መጋሪያ በአሜሪካ ድርጅት ካልተገዛ ሊያግዱት እንደሚችሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።












