ቤላሩስ፡ በተቃውሞው በፖሊስ የተያዙት የ73 ዓመቷ አዛውንት

ታትሟል

አውሮፓዊቷን አገር ቤላሩስን ለረዥም ጊዜ ያስተዳደሩትን ፕሬዚደንት አሌክሳንደር ሉካሸንኮ ከሥልጣን እንዲወርዱ ለመጠየቅ በዋና መዲናዋ ሚንስክ አደባባይ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለፀ።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል በተቃውሞው ላይ ምልክት ወይም አርማ እየሆኑ የመጡት የ73 ዓመቷ አያት ኒና ባሂንስካያ አንዷ ነበሩ።

ቤላሩስን ለ26 ዓመታት ያስተዳደሩት ፕሬዚደንት አሌክሳንደር ነሐሴ ወር ላይ በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በከፍተኛ ድምፅ አሸንፈዋል መባሉን ተከትሎ መጀመሪያ አካባቢ የተካሄዱ ተቃውሞዎች ላይ የተወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ሕዝባዊ ቁጣን ቀስቅሷል።

ሕዝባዊ ተቃውሞው ለ6 ተከታታይ ሳምንታት እሁዶች ይቀጥላል ተብሎም ይጠበቃል።

በየሳምንቱ እሁድ ሰልፍ ለማካሄድ በጀመሩበት የቅዳሜ ዕለቱ ሰልፍ ላይም ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተቀላቅለዋል።

አብዛኞቹም ሴቶች ናቸው።

ይሁን እንጅ ከፖሊስ ጋር በመጋጨታቸው ፖሊስ መንገዳቸውን የዘጋባቸው ሲሆን ተቃዋሚዎቹንም አንድ በአንድ በመያዝ በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተገልጿል።።

በወቅቱም በርካታ ተቃዋሚዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋሉም የፖሊስ መኪናዎች ቦታ እጥረት በማጋጠሙ የተወሰኑ ሰዎችን መልቀቁን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የ73 ዓመቷ ተቃዋሚም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው የነበረ ሲሆን ወዲያው መለቀቃቸው ተዘግቧል።

በአንድ ገለልተኛ በሆነ ድረ ገፅ ላይ የወጡ ምስሎች እንደሚያሳዩት ጭምብል ያጠለቁ ፖሊሶች አዛውንቷ በእጃቸው የያዙትን ሰንደቅ ዓላማና አበባ በመንጠቅ ወደ ፖሊስ መኪናው እንዲገቡ ሲገፏቸው ያሳያል።

በቅዳሜ እለቱ ተቃውሞ ከ300 በላይ ሴቶች መታሰራቸውን የአካባቢው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን አስታውቋል።

ፖሊስ ግን ምን ያህል ተቃዋሚዎችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ በቁጥር አልገለፀም።