አሜሪካ፡ ዶናልድ ትራምፕ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ለመሾም ቃል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በሞት የተለዩትን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሩት ቤደር ጊንስበርግ ለመተካት በሚቀጥለው ሳምንት ሴት ዳኛ እንደሚሾሙ ተናገሩ።
ይህ ንግግራቸውም የፖለቲካ ውዝግብ አስነስቷል።
የ87 ዓመቷ የቀድሞ ዳኛ ጊንስበርግ ሕይወታቸው ያለፈው ምርጫው ለመካሄድ ሳምንታት ሲቀሩት ነው።
የዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኝ ዲሞክራቱ ጆ ባይደን፤ ዳኛዋን በሌላ የመተካቱ ውሳኔ ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ድረስ መቆየት አለበት ብለዋል።
በአሜሪካ ሕግ የዘጠኙ የፍርድ ቤት ዳኞች የርዕዮተ ዓለም ሚዛን መመጣጠን ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን ለማሳለፍ ጠቃሚ ሚና ይጫወታል።
ይሁን እንጅ ፕሬዚደንት ትራምፕ ጊንስበርግን የሚተኩትን ዳኛ ያለምንም መዘግየት እንደሚሾሙ ቃል ገብተዋል።
ፕሬዚደንቱም በሟቿ ዳኛ ምትክ ወግ አጥባቂ ዳኛ ሊሾሙ ይችላሉ የሚል ፍራቻ አለ። ይህም ሪፐብሊካኖች ድምፅ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል በሚል የሰጉ ዲሞክራቶችን አስቆጥቷል።
" በሚቀጥለው ሳምንት አራተኛዋን እጩ አቀርባለሁ። ሴት ነው የምትሆነው" ሲሉ ነበር ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት በሰሜን ካሮሊና ፋየቴቪሌ የምርጫ ዘመቻ ላይ የተናገሩት። "ሴት መሆን እንዳለባት አስባለሁ ምክንያቱም ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን በበለጠ እወዳለሁ" ነበር ያሉት ትራምፕ።
በዚህ ወቅትም የተወሰኑ ደጋፊዎቻቸው በአንድ የፕሬዚደንትነት ዘመን የሕይወት ዘመን ሦስተኛዋን ሴት ዳኛ ለመሾም ያለውን አጋጣሚ እንዲጠቀሙ በማሳሰብ ሃሳባቸውን ደግፈዋል።
ቀደም ብሎ ፕሬዚደንት ትራምፕ በፌደራል የይግባኝ ፍርድ ቤቶች የሚያገለግሉ ሁለት ሴት ዳኞችን አድንቀዋል። ሁለቱ ዳኞች ማለትም ኤሚ ኮኔይ ባሬት እና ባርባራ ላጎኣ ደግሞ ወግ አጥባቂዎች ናቸው።
እነርሱን እንደ አማራጭ ሳይመለከቱ እንዳልቀረም እየተነገረ ነው።
ዲሞክራቶች ግን ከአራት ዓመታት በፊት ዲሞክራቱ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ለአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቧቸውን እጩ ዳኛ የሪፐብሊካኑ ምክር ቤት አግዶ እንደነበር በማንሳት ከምርጫው በፊት የሚደረገውን ሹመት አጥብቀው ተቃውመዋል።
በዚያ ጊዜ የምክር ቤቱ የአብዛኞቹ አባላት መሪ ሚች ማክኮኔል ውሳኔውን ያስተላለፉት የምርጫ ዓመት በመሆኑ እንደሆነ ተናግረው ነበር።
ይሁን እንጅ አርብ ዕለት ሴናተር ሚች፤ ትራምፕ ለቦታው የሚሾሟቸውን እጩ ተቀብለው ከምርጫው ቀን በፊት ምክር ቤቱ ድምፅ እንዲሰጥበት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ጊንስበርግ የሊበራሎች የትግል አርማና ለሴቶች መብት ታከተኝ ሳይሉ የታገሉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
በአሜሪካ ታሪክም ጠቅላይ ፍርድቤቱን በመምራት ሁለተኛዋ ሴት ዳኛ ነበሩ።
በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው መኖሪያ ቦታቸው ወዳጅ ዘመድ በተሰበሰበበት ባጋጠማቸው የካንሰር ሕመም ማረፋቸውን የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አርብ ዕለት ምሽት ደጋፊዎቻቸው በፍርድ ቤቱ አካባቢ በመሰባሰብ አስበዋቸዋል።












