የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ በ87 ዓመታቸው አረፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሩት ቤደር ጊንስበርግ በካንሰር ሕመም ምክንያት በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ጊንስበርግ በአሜሪካ የፍትህ ታሪክ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸውና ለሴቶች መብት ታከተኝ ሳይሉ የታገሉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
ጊንስበርግ ባጋጠማቸው የካንሰር ሐሕመም ምክንያት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ቤታቸው ወዳጅ ዘመድ በተሰበሰበበት በሰላም ማረፋቸውን የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከወራት በፊት ጊንስበርግ ከካንሰር ሕመማቸው ለማገገም የጨረር ህክማና [ኪሞቴራፒ] እንደጀመሩ አሳውቀው ነበር።
ሴትዬዋ በአሜሪካዊያን ዘንድ የሊበራሎች ትግል አርማ ተደርገው ይቆጠራሉ።
ጊንሰበርግ በዕድሜ ትልቋ ዳኛና በአሜሪካ ታሪክ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን በመምራት ሁለተኛዋ ሴት ነበሩ።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጆን ሮበርትስ የጊንስበርግን መሞት ተከትሎ “አገራችን ታሪካዊ የሕግ ሰው አጥታለች” ብለዋል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ካሉ አራት ዳኞች አንዷ የሆኑት ጊንስበርግ የጤናቸው ሁኔታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ማን ይተካቸዋል የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሟቿ ዳኛ ምትክ ወግ አጥባቂ ዳኛ ይተካሉ የሚል ፍራቻ አለ።
ይህ ደግሞ ኅዳር ላይ ከሚካሄደው ምርጫ በፊት መሆኑ ለዴሞክራቶች የሚዋጥ አልሆነም።
ጊንስበርግ ከመሞታቸው በፊት ይህን መሰል እርምጃን እንደማይደግፉ በግልፅ አሳውቀው ነበር።
"የእኔ ምኞት አዲስ ፕሬዝደንት ሳይመረጥ አዲስ ዳኛ በምትኬ እንዳይሾም ነው" ሲሉ ለልጅ ልጃቸው በፃፉት ደብዳቤ ላይ አሳውቀው ነበር።
ነገር ግን ትራምፕ ወዲያውኑ ወግ አጥባቂ ዳኛ ለመሾም ዕቅዳ እንዳላቸው ከዋይት ሐውስ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ትራምፕ የሴትዬዋን ሞት የሰሙት ለምርጫ ቅስቀሳ ሚኒሶታ በተገኙበት ወቅት ነው።
ዜና እረፍቱን ከጋዜጠኞች የሰሙት ትራምፕ፤ "አላወቅኩም ነበር። በጣም አስገራሚ ሕይወትን የመራች ሴት ናት። ሌላ ምን ማለት እችላለሁ?" ካሉ በኋላ ወደ አውሮፕላናቸው አቅንተዋል።
ጊንስበርግ በተለያዩ የካንሰር ሕመሞች ምክንያት ጤናቸው ተቃውሶ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ጊዜያት ሆስፒታል ገብተው ሕክምና አግኝተዋል።
የሴትዬዋ ዜና እረፍት ከተሰማ በኋላ ማን ይተካቸው? አሁን መተካት አለባቸው ወይ? በሚሉ ሐሳቦች አሜሪካ ተከፋፍላለች።
















