ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩዋንዳ ፡ የ'ሆቴል ሩዋንዳ' ፊልም ጀግና ፍርድ ቤት ቀረቡ
በጎርጎሮሳዊያኑ 1994 የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ወቅት በፈፀሙት በጎ ተግባር 'ሆቴል ሩዋንዳ' የተባለውን ፊልም ሆሊውድ እንዲሰራው ምክንያት የሆኑት ፖል ሩሴሳባጊና ፍርድ ቤት ቀረቡ።
የ66 ዓመቱ ፖል ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው በኋላ በፖሊስ ታጅበው፣ እጃቸው በካቴና ታስሮ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ላይ የታዩት ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር።
ዝነኛው ፖል ክስ የቀረበባቸው በደቡብ ምዕራብ ሩዋንዳ በሚገኘው ብሔራዊ ነፃነት ግንባር [ኤፍ.ኤል.ኤን] በ2018 እና 2019 ከፈፀመው ጥቃት ጋር ተያይዞ ነው።
ግንባሩ የኤም.አር.ሲ.ዲ- ኡብምዌ የተባለና በውጭ የሚገኝ የሩዋንዳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መድረክ የጦር ክንፍ ነው። ፖልም የዚህ መድረክ ምክትል ፕሬዚደንት ናቸው።
ፖል በቀረበባቸው ክስ ላይ ምንም አስተያየት አልሰጡም።
ዛሬ ፍርድ ቤት ሲቀርቡም በችሎቱ ከፍተኛ ጥበቃ የነበረ ሲሆን፤ ችሎቱን የተከታተሉትም የተመረጡ ጋዜጠኞች ብቻ ናቸው። ጋዜጠኞቹ ወደ ፍርድ ቤቱ እንዲገቡ ከመፈቀዱ በፊት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸዋል ተብሏል።
የፖል ቤተሰቦችም በሩዋንዳ ካሉ ጠበቆች በተጨማሪ እርሳቸውን ወክለው የሚከራከሩ ዓለም አቀፍ ጠበቆችን ያዘጋጁላቸው ቢሆንም፤ በሩዋንዳ እርሳቸውን ወክለው እንዲከራከሩ አልተፈቀደላቸውም።
ፖል በስደት በአሜሪካ ይኖሩ የነበሩና የቤልጂየም ፓስፖርት ያላቸው ሁለት በአገር ውስጥ የሚገኙ ጠበቆችን መምረጣቸውን የሩዋንዳ መንግሥት አስታውቋል። ይሁን እንጂ ቤተሰቦቻቸው የጠበቆቹ ምርጫ እና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
ፖል የተያዙበት ሁኔታም ቤተሰቦቻቸውንና መንግሥትን ያስማማ አይደለም።
የፖል ቤተሰቦች ፖል ከዱባይ እንደተጠለፉ የተናገሩ ሲሆን መንግሥት ግን ሩዋንዳ በሄዱበት እንደታሰሩ ገልጿል።
በጎርጎሮሳዊያኑ 2014 ለዕይታ የበቃው 'ሆቴል ሩዋንዳ' ፊልም፤ መካከለኛ ገቢ ያላቸው የሁቱ ጎሳ ፖል ሩሴሳባጊና፤ የቱትሲ ተወላጅ አግብተው ይኖሩ ነበር።
ፖል ዘር ጭፍጨፋ የሚፈፅሙ የሁቱ ሚሊሻዎችን ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን በመጠቀም እና በገንዘብ በመደለል እስከ 1200 የሚሆኑ ቱትሲዎች ደኅንነቱ የተጠበቀ ማምለጫ እንዲያገኙ በማድረግ ሲያተርፉ ያሳያል።
በዚህ ፊልም ላይ ፖልን ወክሎ የተጫወተው አሜሪካዊው ተዋናይ ዶናልድ ፍራንክ ቺድሌ ነበር።
በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ 800 ሺህ የሚጠጉ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ተገድለዋል።