ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩዋንዳ የጸጥታ ኃይል '19 ሽብርተኞችን' መግደሉን አስታወቀ
የሩዋንዳ የፀጥታ ኃይሎች ለ14 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነ ጥቃት ፈፅመዋል ያሏቸውን 19 አሸባሪዎች መግደላቸውን አስታወቁ። ባሳለፍነው አርብ በአገሪቷ ሰሜናዊ ክፍል የተፈፀመው ጥቃት በሁቱ አማጺያን እንደሆነ ታውቋል።
አማጺያኑ ጥቃቱን ያደረሱት ለምግብ ፍለጋ በተሰማሩበት ጊዜ ሳይሆን እንዳልቀረ ባለሥልጣናት ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልፀዋል።
ባሳለፍነው አርብ እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች የተለያዩ ስለታማ ነገሮችን፣ ዱላ እና ድንጋይ በመያዝ የጎሬላ ዝንጀሮ መገኛ በሆነው ታዋቂው የእሳተ ገሞራ ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢ በሙሳንዜ ግዛት በመሄድ ነበር ጥቃቱን የፈፀሙት።
በወቅቱ የሟቾቹ ቁጥር ስምንት እንደሆነ ቢነገርም፤ አሁን ላይ ግን ቁጥራቸው 14 እንደደረሰ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
አካባቢው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የሁቱ አማጺያን ኢላማ ተደርጎ ነበር።
እነዚህ አማጺያን በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1994 በሁቱ የሚመራው የዘር ጭፍጨፋ በቱትሲዎች ላይ ከደረሰ በኋላ የተቋቋመውን የዲሞክራቲክ ኃይል ለነፃናት [ኤፍ ዲ ኤል አር] ሚሊሻ የተካተቱበት ነበር።
የአገሪቷ ፖሊስ የወሰደው የአፀፋ እርምጃ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ድንበር አቅራቢያ እንደተፈፀመ ፖሊስ አስታውቋል።
የሩዋንዳ ፖሊስ እንዳስታወቀው የተወሰኑት ወንጀለኞች ላይ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ነበር። "የፀጥታ ኃይሎች እነዚህን ሽብርተኞች ሲከታተሉ ቆይተዋል። በዚህም መሠረት አስራ ዘጠኙ ሲገደሉ፤ አምስቱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል" ሲል ፖሊስ አስታውቋል።
የቱሪዝም ሚንስትር በበኩሉ በአካባቢው የነበሩ ጎብኚዎች ላይ የደረሰ ምንም ጉዳት እንደሌለ ገልጿል።