ቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቼን አሜሪካ "በማን አለብኝነት እያስፈራራቸው" ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ቲክቶክ፣ ዊቻት በአሜሪካ መታገዳቸውን ተከትሎ ቻይና ኩባንያዎቿ ግልፅ የሆነ "የማስፈራሪያ ጥቃት" በአሜሪካ እየደረሰባቸው ነው ብላለች።
የቻይና መንግሥትም "በአሜሪካ የበላይነትና ማን አለብኝነት" ብሎ በጠራው የተፈጠረውን ጫና ለማስተካካልም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን የሚገዛ አለም አቀፍ መመሪያዎችን አውጥታለች።
በአዲሱ ጅማሮ መሰረት የዜጎችን የግል መረጃ በህገወጥ መንገድ መሰብሰም ሆነ በዜጎች ላይ የሚደረግ ከፍተኛ ስለላና ክትትል ህጋዊ አይደለም በማለት አስምሯል።
በባለፈው ወርም እንዲሁ መረጃዎችን ከመጠበቅና ደህንነት ጋር ተያይዞም አሜሪካ "ክሊን ኔትወርክ" (ከማንም ነፃ የሆነ ኔትወርክ) የሚል እሳቤን አስተዋውቃለች።
የመረጃን ደህንንነት በተመለከተ እሰጣገባ የገቡት አሜሪካና ቻይና ፤ ቲክቶክ፣ ሁዋዌና ዊ ቻትም መወዛገቢያ ሆነዋል።
በቅርብ ወራትም የትራምፕ አስተዳደር የቻይና የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭና ተንቀሳቃሽ ስልኮች አምራች ሁዋዌን ጨምሮ የማህበራዊ ሚዲያዎቹን ቲክቶክና ዊቻት ብሄራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ ይጥላሉ በሚል አግዷል።
"አንዳንድ ሃገራት በማን አለብኝነትና በትምክህተኝነት አገራትን ሲያዋርዱ ይታያሉ። መረጃን በመጠበቅና ደህነነት በሚል ሽፋንም በአለም እየመሩ ያሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ለማጥቃት አነጣጥረዋል" በማለት የቻይና መንግሥት አማካሪ ዋንግ ይ ተናግረዋል።
"ይሄ ግልፅ ያለ ማስፈራራትና ጉልቤነት ነው። ልንቃወመው ይገባል" ብለዋል።
ዋንግ በዛሬው እለት እንደተናገሩት ቻይና ያወጣቻቸው አዳዲስ መመሪያዎች ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የግል መረጃዎቻቸውንና አገልግሎታቸውን ለተለያዩ ኩባንያዎች አስተላልፈው እንዳይሰጡም ጥሪ አድርጓል።
አሜሪካ በበኩሏ የቻይናው ቴሌኮም አገልግሎት ሰጭና ተንቀሳቃሽ ስልኮች አምራች ኩባንያ ሁዋዌ በስልኮቹ ላይ መረጃዎችን አሳልፎ የሚሰጥ የተገጠመ ማሽን አለው በማለት ትወነጅላለች።
"የአለም አቀፉ መረጃ ደህንነት ሁሉም አገራት በመከባበር፣ በመተሳሰብና አለም አቀፍ ተሳትፎን መሰረት ያደረገ ነው" በማለት ዋንግ አስረድተዋል።












