ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእንስሳት ደህንነት፡ በፈረንሳይ የፈረሶችን አካላት እየቆራረጠ የሚገድለው ተጠርጣሪ ተያዘ
በፈረንሳይ የፈረሶችን አካል የሚቆራርጠው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ፖሊስ አሳውቋል።
በቅርብ ወራት ውስጥ ምስጥራዊ በሆነ ሁኔታ በርካታ ፈረሶች አካላቸው ተቆራርጠው እንዲሁም ተገድለው በመገኘታቸው ምርመራ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ የአምሳ አመት ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል።
በሰሜን ምዕራብ በሚገኘው ዲጆን ግዛት ጋር በደረሰ የፈረሶች ጥቃት ላይ ተጠርጥሮ የተያዘው ግለሰብ በአካካቢውም ሲያንዣብብ ከታየ በኋላ ነው።
በባለፉት ወራት ከሰላሳ በላይ ፈረሶች ተቆራርጠው ተገድለዋል፤ እንዲሁም አንዳንዶቹ የሰውነት ክፍላቸው ተቆራርጦ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል።
በቅርቡም የደረሰው ጥቃት በደቡብ ዲጆን ግዛት እሁድ ዕለት ተፈፀመ የተባለው ነው።
ባለቤቱ በፈረሶቹ ማደሪያ አካባቢ የፋኖስ መብራት የያዘ ሰው ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ በማየቱ ለፖሊስ ደውሏል።
ምንም እንኳን በዚህ አጋጣሚ ፈረሱ ከፍተኛ ጉዳት ባይደርስበትም ከዚህ ቀደም ጆሯቸውና ብልታቸው የተቆራረጡ በርካታ ፈረሶች ተገኝተዋል።
ፈረሶች የጥቃት ኢላማ ለምን ሆኑ ለሚለው ፖሊስ ምንም አይነት መላምት መስጠት አልቻለም።
ከዚህም በተጨማሪ አንድ ግለሰብ ፈረሶቹን እያጠቃ ይሁን በቡድን ተደራጅተው እየተጠቁ ይሁን ለሚለውም ገና ምርመራ ያስፈልገዋል ተብሏል።
ተጠርጣሪው ከእሁዱ ጥቃት ጋር በተያያዘ ጀርመንና ፈረንሳይን በምታዋስነው የድንበር ከተማ ናምብሼይም የተገኘ ሲሆን ፖሊስ ስሙን ከመግለፅ ተቆጥቧል።
አቃቤ ህግ በበኩሉ የተጠርጣሪውን ማንነት አስመልክቶ በሰጠው መረጃ ግለሰቡ ስራ የሌለውና በጀርመንም በርካታ እንስሳት ላይ ጥቃት በማድረስ የታወቀ ነው ብሏል።
በመጀመሪያ ቤቱ ላይ በተደረገው ምርመራ ጠንከር ያለ መረጃ ባይገኝም በርካታ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች በመገኘታቸው እነሱን ማጣራት ያስፈልጋል ተብሏል።