ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዝንብ ፡ በአንዲት ዝንብ የተበሳጩት አባት ጉዳት ደረሰባቸው
ዝንብ ሲያሳድዱ የነበሩት አዛውንት መኖሪያ ቤታቸውን በእሳት አጋዩ።
ነገሩ ፈረንሳይ አገር ውስጥ ነው የሆነው። የ80 ዓመት ሽማግሌ ናቸው። እራት ሊበሉ ሲሉ አንዲት ዝንብ ረበሸቻቸው።
ወደ ጆሯቸው እየተጠጋች አቀወሰቻቸው። የ80 ዓመቱ ሽማግሌ ተበሳጩ።
ዝንቧን ሊገድሏት ሲሉ ግን እያመለጠች አስቸገረቻቸው።
የምታሰማው ድምጽ እሳቸውን ለማበሳጨት ሆን ብላ ይመስላል። አንዳች ተልእኮ የተሰጣት ይመስል ልክ እራት ሊበሉ ሲሉ ነው እየመጣች 'የምትነጅሳቸው'።
በዚህን ጊዜ ዝንቦችን በኤሌክትሪክ አቃጥሎ የሚገድለውን የኤሌክትሪክ ወንፊት ለኮሱ።
ለኩሰው ካጋሉት በኋላ በኤሌክትሪክ ወንፊቱ ዝንቧን ለመቅለብ ሲሞክሩ በአቅራቢያ የነበረውን የጋዝ ሲሊንደራቸውን ገለበጡት።
በዚህን ጊዜ የጋዝ ሲሊንደሩ ማፍሰስ ጀመረ። ዝንብ አድኖ መግደያ የኤሌክትሪክ ወንፊቱ ከጋዝ ሲሊንደሩ ጋ ንክኪ ፈጠረና ቤቱ ውስጥ ከባድ ፍንዳታ ተከሰተ።
ፍንዳታው የሰውየውን ማድቤት፣ የዋና ቤቱን ጣሪያና የቤት እቃዎችን ሙሉ በሙሉ አውድሟል።
ሽማግሌው ታዲያ እድለኛ ናቸው።
ከሞት አምልጠዋል። የተወሰነ እጃቸውን በእሳት ቢለበለብም ለክፉ አልሰጣቸውም። ሕክምና ተወስደዋል።
ሽማግሌው አሁን ከሆስፒታል ወጥተዋል። ቤቱ እስኪታደስላቸው ጫካ ሄደው ድንኳን ቀልሰው መኖር ጀምረዋል።
ይህን ሁሉ መአት ያመጣችባቸው ዝንብ ግን የደረሰችበት አልታወቀም።